Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሃመድ የተመራ የመንግሥታቱ ድርጅት ልዑክ በኮምቦልቻ ጉብኝት አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ የተመራ የመንግሥታቱ ድርጅት ልዑክ ኮምቦልቻ ከተማ በመግባት አሸባሪው የህወሀት ወራሪ ቡድን የፈጸመውን ውድመት ተመለከቱ ፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሃመድ አሸባሪው የህወሀት ወራሪ ቡድን በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ያደረሰውን ውድመት እና የአካባቢውን ንጹሃን ተወላጆች በጅምላ ከጨፈጨፈ በኋላ በኮሌጁ ግቢ በጅምላ የቀበራቸውን የቀብር ስፍራ ተመልክተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር እና የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በምክትል ዋና ጸሐፊዋ የተመራው ልዑክ በህወሃት የሽብር ቡድን የወደሙ አካባቢዎችን ከጎበኘ በኋላ÷ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ቡድን በኮሌጁ ላይ ስላደሰው ሁለንተናዊ ውድመትና ዘረፋ እንዲሁም ስለፈጸመው ጭፍጨፋ ለምክትል ዋና ጸሀፊዋ ገለጻ አድርገዋል።

ምክትል ዋና ጸህፊዋ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከአመራሩና የተለያየ ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች፣ ህጻናትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል ።

ምክትል ዋና ጸህፊዋ በሽብር ቡድኑ የወደሙ ሌሎች ተቋማትንም ተዘዋውረው ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በፀጋዬ ወንድወሰን እና ይከበር አለሙ

Exit mobile version