አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እስካሁን 10 ሚሊየን ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸውን በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ገለጹ፡፡
10 ሚሊየን ያህል ዜጎች መከተባቸውን የገለጹት አስተባባሪው÷ በቀጣይ የክትባት ዘመቻዎች እስከ 20 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ክትባት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ዋና አስተባባሪው ዶክተር መብራቱ ማሴቦ ።
እስካሁን እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑት ሲሰጥ የነበረው ፋይዘር ክትባት በዚህ ዘመቻ በትምህርት ላይ ለሚገኙ፣ በሁለተኛ ደረጃ እና በዩኒቨርሲቲ ላሉ ተማሪዎች ጥቅም ላይ እደሚውልም ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ሲኖፋርም እና በአንድ ዙር የሚሰጠውን ጆንሰን በበርካታ ቁጥር ሀገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ በስራ ምክንያት ክትባቶቹን ሳይወስድ እንዳይቀር በእርሻ ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በገበያዎችና በመሳሰሉት ቦታዎች ክትባቱን እንዲያገኝ ዘመቻ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቅርቡ የሰሞኑ ጉንፋን ሲባል የነበረው አራተኛው ማዕበል መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው÷ በዓለም ጤና ድርጅት ስያሜ የተሰጣቸው አራቱ ማዕበላት አልፋ፣ ቤታ፣ ዴልታ እና አሁን ኦሚክሮን ናቸው ብለዋል።
በሁለተኛው ማዕበል ክትባቱ ከመጀመሩ በፊት አብዛኛው ሰው ሆስፒታል ይገባ ነበር፤ በቀን የሚሞተው ሰው እስከ 50 ደርሶ እንደነበር አስታውሰው በአራተኛው ማዕበል የተያዘው ሰው ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ በቀን በአማካይ የሚሞተው ሰው ቁጥር ከ20 እንደማይበልጥና በዚህም በዋነኝነት ክትባቱ ከፍተኛ የሞት ቁጥር መቀነሱን አመላክተዋል።
በመሆኑም ክትባቱ በቂ የመከላከል አቅም መፍጠሩን በአገራችን በጥናት የተረጋገጠ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
አሁንም ወረርሽኙ ጨርሶ ያልወጣ መሆኑን ጠቁመው÷ በቀጣይ ግንቦት እና ሚያዝያ ወራት የአምስተኛው የኮቪድ-19 ማዕበል ስጋት መኖሩን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

