አዲስ አበባ፣የካቲት 2፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ አዲስ መኪና ለመረከብ ለ “ኢ ኤል አውቶ መኪና አስመጪ ድርጅት” 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ብንከፍልም መኪኖቹን ባለመረከባችን ቤተሰቦቻችን ለችግር ተጋልጠዋል ሲሉ የቀድሞ የላዳ ሹፌሮች ቅሬታ አሰሙ፡፡
ለበርካታ ዓመታት በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁት በተለምዶ “ላዳ ታክሲ” ተብለው የሚጠሩት መኪኖች ለአዲስ አበባ እድገት እና ዘመናዊነት ስለማይመጥኑ መኪኖቻቸውን በአዲስ እንዲቀይሩ ከተማ አስተዳደሩ መወሰኑ ይታወሳል።
ውሳኔውን ተከትሎ በ “ላዳ” ዎቻቸው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት አሽከርካሪዎች ሃያ በመቶ ቅድመ ክፍያ ከፍለው በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ አዳዲስ መኪኖች ለመረከብ ከ “ኢ ኤል አውቶ መኪና አስመጭ ድርጅት” ጋር ውል ማሰራቸውን ይናገራሉ፡፡
አሽከርካሪዎቹ ÷ድርጅቱ በውላችን መሠረት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ መኪኖቹን ገዝቶ ባለማስረከቡ ምክንያት ሥራ ሠርተን ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ማስተዳደር አልቻልንም ብለዋል።
መኪኖቹን ለማስመጣት ውል የገባው የ“ኢ ኤል አውቶ መኪና አስመጭ ድርጅት” ሥራ አስኪያጅ በቀለ አበበ በበኩላቸው÷ እስካሁን 6 መቶ መኪኖችን እንዳስመጡ ተናግረው፥ አዲስ መመርያ እና ደንብ በመውጣቱ ምክንያት ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተፈቀዱልን መኪኖች ታግደው ከወደብ ማውጣት አልቻንልም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ በበኩላቸው ÷ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑንና ከባንክ እና ከጉምሩክ ጋር ያሉ ሂደቶችንም በፍጥነት ጨርሰው ችግሩ እልባት እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡
በሲሳይ ጌትነት

