Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፋር ክልል በወራሪው ህወሓት እየተፈናቀሉ ለሚገኙ ዜጎች አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋል -ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ቡድን ዳግም ወረራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአፋር ክልል ነዋሪዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጹ።
 
በዶክተር ዲማ ነገዎ የተመራው የቋሚ ኮሚቴው ቡድን ሰሞኑን በአፋር ክልል የመስክ ምልከታ አድርጓል።
 
ቡድኑ ለትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑት የአፋር ክልል 14 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአፍዴራ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጎጂዎችንና የአከባቢው አመራሮችን አነጋግሯል።
 
ተፈናቃዮቹ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባደረሰባቸው የከባድ መሳሪያ ድብደባ መኖሪያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ገልጸዋል።
 
በተጨማሪም የት እንዳሉ ያልታወቀ በርካታ ዜጎች ስለመኖራቸው ነው ተፈናቃዮች ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ያስረዱት።
 
የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንን ጨምሮ ከተለያዩ ለጋሾች ሲደርስ የነበረው ሰብዓዊ ድጋፍም በአሸባሪው ቡድን ቁጥጥር ስር መዋሉን ከአብአላ ወደ አፍዴራ የተፈናቀሉ ዜጎች ጠቁመዋል።
 
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋውረው በአሸባሪው ቡድን ከቀያቸው ተፈናቅለው መንገድ ላይ የወለዱ እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካሞች እንዲሁም በጥቃቱ ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትን ተመልክተዋል።
 
የአፋርን ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በጦርነት መግጠም የማይደፍረው የህወሓት ሃይል ሰላማዊ ዜጎች ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን የአከባቢው አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።
 
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ባደረጉት ምልከታ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በአሸባሪው ቡድን የከባድ መሳሪያ ጥቃት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ቁስለኞችን ጎብኝተዋል።
 
ጉብኝቱን ተከትሎም አባላቱ ከሃይማኖት መሪዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
 
መንግስትና የተለያዩ ለጋሾች ለአፋር ክልል እያደረሱ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የክልሉ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች÷ የተከፈተባቸው አዲስ ጥቃት በከባድ መሳሪያ የታገዘ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ ብቻውን ሊቋቋመው እንደማይችል ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።
 
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በክልሉ እየተፈናቀለ እና አየሞተ ለሚገኘው ህዝብ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
 
ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሩ እልባት ለመስጠት ይሰራል ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version