Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“ሠራዊቱ ተንከባክቦ ለሕክምና አብቅቶናል፤ ከሞትም ታድጎናል”

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሽብር ቡድኑ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች አሸባሪ ቡድኑ “ለመናገር ቀርቶ ለማሰብ የሚከብድ ግፍ” እንደፈጸመባቸው ይገልፃሉ፡፡

በሽብር ቡድኑ ጉዳት ደርሶባቸው ጦር ኃይሎች ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ጥግ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ እንዳመጣቸውም ተጎጂዎቹ ተናግረዋል፡፡

የ27 ዓመት ወጣት የሆነችው ወርቄ ወዳጄ፥ የአምሥት እና የአንድ ዓመት ከሦስት ወር እድሜ ያላቸው ሕጻናት እናት እንደሆነችና ሕዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በሯን ገንጥለው በመግባት አሰቃቂ ግፍ እንደፈጸሙባት አስረድታለች፡፡

“እያለቀስኩ ብማጸናቸውም በጀርባዬ ያዘልኩትን ህጻን ልጄን ነጥቀው በመወርወር እኔን መታገል ጀመሩ ፣ ይህን ሁሉ ግፍ የሚፈጽሙት እጅና እግሩን ባሰሩት ባለቤቴ ፊት ነው” ስትልም ነው የሽብር ቡድኑን ታጣቂዎች ጭካኔ የገለጸችው፡፡

“ሊይዙኝ ሲታገሉ እምቢ ስላልኳቸው በጥይት ግራ እግሬን መትተው ጣሉኝ” ፣ ባለቤቴ እኔን ሊያተርፍ ከታሰረበት ገመድ ጋር መታገል ሲጀምርም በጥይት ሩምታ እኔና ልጆቼ ፊት ገድለውት ሄዱ” ስትልም ነው የተናገረችው፡፡

የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ መንገሻም በተመሳሳይ የአሸባሪ ቡድኑ ግፍ ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዷ ናቸው፡፡

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በአካባቢው በወረራ በቆዩባቸው ጊዜያትም ወደ ቤታቸው በመምጣት ለልጆቻቸው የጋገሩትን እንጀራ ከህጻናት ጉሮሮ እየነጠቁ ይመገቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አንድ ቀንም እንጀራ ለመጋገር በሌሊት በተነሱበት አጋጣሚ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በጥይት ሩምታ በመክፈት እጃቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ይናገራሉ፡፡

ወጣት ሀዲጋዝ ራህመት ደግሞ “ቤት ውስጥ በተቀመጥንበት መጥተው ካስወጡን በኋላ የሚገድሉትን ገድለው ያቆሰሉትን አቁስለው ጥለውን ሄዱ” በማለት በእርሷና ቤተሰቦቿ ላይ የደረሰውን ግፍ ትናገራለች፡፡

በተተኮሰባቸው ጥይትም በእጇ የየዘችው የአራት ዓመት ህጻን ሕይወቱ ሲያልፍ በጀርባዋ ያዘለችው ጨቅላ ህጻን ደግሞ ክፉኛ ተጎድቶ በሕክምና ላይ እንደሚገኝ ተናግራለች፡፡

ወጣት ሀዲጋዝ ÷ በግራ ጉንጯ ላይ ክፉኛ የተጎዳች ሲሆን፤ “ወጣትነቴን ቀሙኝ” ስትል በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የደረሰባትን ጭካኔ አስረድታለች፡፡

ተጎጂዎቹ “የመከላከያ ሠራዊቱ ተንከባክቦ ለሕክምና አብቅቶናል፣ ከሞትም ታድጎናል” ሲሉም ሠራዊቱ ያደረገላቸውን እንክብካቤ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version