አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 397 ቱርክ-ሰራሽ ሽጉጦች፣ 60 የክላሽ ጥይቶች፣ 13 የክላሽ ሰደፍ እንዲሁም አንድ ክላሽ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ መያዙን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የፀጥታ መዋቅር ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል በሕገ ወጥ መንገድ የተደበቁ የጦር መሳሪያዎችንና ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ታውቋል፡፡
የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ኃይሌ ብርሃኑ እንደተናገሩት÷ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት የተደበቁ 397 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች፣ 60 የክላሽ ጥይት፣ 13 የክላሽ ሰደፍ እንዲሁም አንድ ክላሽ ተይዟል።
ሽጉጡ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ጠረፍ ወርቅ በተባለ ቀበሌ የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ላይ በኅብረተሰቡና በፀጥታ መዋቅሩ ክትትልና ፍተሻ መያዙን ነው ረዳት ኢንስፔክተሩ የገለጹት።
አያይዘውም በሕገ ወጥ ንግድ እና የጦር መሣሪያ ዝውውር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።
ሕብረተሰቡም ከፀጥታ ኀይሉ ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!