አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህፃናት አድን ድርጅት በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ፈጽሞት በነበረው ወረራ ለተጎዱ ወገኖችና ተቋማት ድጋፍ የሚውል የ23 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን አበረከተ።
የሽብር ቡድኑ በክልሉ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት የተገኙት በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሽብር ቡድኑ ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት የግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የባለሃብቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ስዩም ፥ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶችም የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ላይ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።
የህፃናት አድን ድርጅት በዞኑ በህፃናት ደህንነትና ስርዓተ ምግብ መሻሻል ላይ ሲሰራ መቆየቱን በህፃናት አድን ድርጅቱ የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አሸብር ደበበ አስታውሰዋል።
ድርጅቱ በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ተቋማት 23 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ማበርከቱን ኢዜአ ዘግቧል።
ለ3 ሆስፒታሎች እና ለ20 ጤና ጣቢያዎች የሚያገለግሉ መድሃኒቶች፣ የህሙማን መኝታ ፍራሾች፣ የተማሪዎች መማሪያ ደብተርና እስክብሪፕቶ ፣ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ፍራሽና ብርድ ልብስ ድርጅቱ ካበረከታቸው ቁሳቁሶች ይገኙበታል ተብሏል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

