Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከበጋ መስኖ ሥራ የተገኘው ውጤት በቀጣይ የገበያ እጥረቱን ሊሸፍን የሚችል ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ያሳየ ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጋ መስኖ ልማት እየተሠራ ያለው ሥራ በመጪዎቹ ዓመታት ሙሉ በሙሉ የገበያ እጥረቱን ሊሸፍን የሚችል ምርት በሀገር ውስጥ መመረት እንደሚቻል ያሳየ ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራ ልዑክ በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ የበጋ ስንዴ ልማት፣ የቡና ክላስተር እና የሙዝ ክላስተርን ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፥ ባለፉት ዓመታት በአማካይ የገበያ እጥረቱን እና ጉድለቱን ለመሙላት የሚጠየቀው ወደ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ መሆኑን ጠቁመው፥ አሁን በበጋ እየተሠራ ያለው የስንዴ ልማት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ጊዜ በመጪዎቹ ዓመታት ሙሉ በሙሉ የገበያ እጥረቱን ሊሸፍን የሚችል ምርት በሀገር ውስጥ መመረት እንደሚችል የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ይህም የሀገር ውስጥን እምቅ አቅም የሚያሳይ እና ለኑሮ ውድነት ችግር የሆኑ የምርትና ምርታማነት ችግሮችን በዚህ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል እንደ ሀገር የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፥ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ዋናው ግብዓታቸው ከግብርና የሚገኝ ምርት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሙዝና የመሳሰሉ ምርቶችን በዚህ መንገድ ማምረት የተጀመሩ የአግሮ ኢንዱስትሪ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ መመጋገብም የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየርና የተጀመረውን የኢንዱስትሪ ልማት በማሳካት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ነው ያሉት፡፡
የሀገሪቱ ችግር የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የበጋ መስኖው ልማት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአንድ በኩል ገቢ ምርትን በመተካት በሌላ በኩል ደግሞ ምርቶቹን በቀጥታ በመሸጥና በማቀነባበር የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በጣም የተሸለ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ወደፊት ኢንዱስትሪውን እና ግብርናውን ማገናኘት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን የሚያሳድግ መሆኑን በማንሳት የታየው ውጤት ትልቅ ተስፋ የተጣለበትና በሁሉም ክልሎች መስፋት ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት የመደጋገፍ ሥራቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ ነው ያሳሰቡት።
በጉብኝቱ የተሳተፉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በበኩላቸው፥ የበጋ መስኖ ሥራ ከውጭ የሚገባውን እህል ለመተካት የሚያስችል ተስፋ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በምርቱ ላይ እሴት ተጨምሮ ለህብረተሰቡ የሚቀርብበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version