Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ 15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ ለመከላከያ ሰራዊት ከ32 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ 15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ በሀገር ውስጥ በጀግንነት እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊታችን 32 ሺህ 410 ዶላር ድጋፍ አደረገ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተደረገው የድጋፍ ርክክብ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል መህዲ ፥ ሰላም አስከባሪ ሻለቃው የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት የሚያኮራ ተልዕኮ እየፈፀመ የህዝብን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር በሀገር ቤት እየተፋለመ ለሚገኘው ጀግናው ሠራዊት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ለሀገሩ ያለውን ያልተቆጠበ ፍቅር የሚያሰይ ነው ብለዋል።

በያምቢዩ እና ታምቡራ የደቡብ ሱዳን ግዛቶች ሰላም አስከባሪ ሻለቃው አመርቂ የግዳጅ አፈጻጸም በማስመዝገብ የአካባቢውን ህብረተሰብ ሰላም በአስተማማኝ ማስጠበቅ ችሏል ያሉት ደግሞ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ ብ/ጄኔራል ዳዊት ወ/ሰንበት ናቸው።

ወታደራዊ አታሼው ፥ ሻለቃው ሀገሩንና ወገኑን በተልዕኮው ከማኩራት በተጨማሪ ለሀገር ቤት ሰራዊት ድጋፍ ማድረጉ የኢትዮጵያ አለኝታነቱን የሚያሳይ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የ15ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ከፍያለው ረጋሳ በበኩላቸው ፥ ግዳጃችንን በአኩሪ ሁኔታ ከመፈፀም ባሻገር በሀገር ውስጥ ከሽብርተኛ ሃይሎች ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው ሠራዊታችን ድጋፍ ማድረግ በመቻላችን ደስተኞች ነን ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version