አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መነሻቸውን ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉ 19 ሺህ 447 ጥይቶች እና ሶስት ሽጉጦች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ከአዲስ አበባ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራ ሊያዙ ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ እንዳመለከተው፥ መነሻውን ከአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ያደረገ አንድ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ በፒካፕ ተሽከርካሪ 4 ሺህ 847 የክላሽ ጥይት ጭኖ መዳረሻውን አዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ በመጓዝ ላይ እያለ በተደረገ ክትትል ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ ሲደርሰ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዘዋዋሪው ከእነጦር መሣሪያው በቁጥጥር ስር ውሏል።
በተመሳሳይ ሌላ ፒካፕ ተሽከርካሪ ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ተጭኖ ወደ ጎንደር እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ 14 ሺህ 500 የክላሽ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ጥይት እና አዘዋዋሪው ደቡብ ጎንደር ዞን ንፋስ መውጫ ከተማ ላይ ከአማራ ፖሊስ ጋር በመተባበር ተይዘዋል፡፡
በሌላ በኩል መነሻውን አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ያደረገ አንድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በእህል ውስጥ 100 የብሬን ጥይቶች እና 3 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ደብቆ በመጫን ለማሳለፍ ያደረገው ሙከራም በጸጥታ ሃይሎች ከሽፏል፡፡
በተመሳሳይ መዳረሻውን ደቡብ ክልል ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ለማድረግ በመጓዝ ላይ በነበረው ህገወጥ መሣሪያ ላይ በተደረገው ክትልል አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዘዋዋሪው ከነጦር መሣሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
ህገወጥ የጦር መሣሪያዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና መጫወቱ የተመላከተ ሲሆን፥ ይኸው እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል፡፡

