አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መድኃኒትና የህክምና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ክልል መድረሳቸውን እና 107 ሜትሪክ ቶን ተጨማሪ መድኃኒት ለማድረስ ዝግጅት ተጠናቆ የካርጎ በረራ እየተጠበቀ መሆኑን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ፈቃድ ባገኙ ሰብዓዊ ድርጅቶች አማካኝነት ከጥር ወር ጀምሮ መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች እየደረሳቸው መሆኑን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደትም በረድዔት ሥራ የተሰማሩ ኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ኦፍ ሬድ ክሮስ፣ ዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፣ ፕላን ኢንተርናሽናል፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ሴቭ ዘ ቺልድረን እና ዩኒሴፍን ጨምሮ ስምንት ያህል ተቋማት ወደ ትግራይ ክልል መድኃኒት ማስገባታቸው ተረጋግጧል ብለዋል።
ባለፈው ሣምንት ብቻ በኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ኦፍ ሬድ ክሮስ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ አማካኝነት 41 ሜትሪክ ቶን መድኃኒትና የህክምና ግብዓቶች መቀሌ መድረሳቸውንም ነው ለኢፕድ የተናገሩት፡፡
ከተላከው በተጨማሪም የክትባትና ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን ጨምሮ 107 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት ለማድረስ የካርጎ በረራ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
ድጋፍ አቅራቢ አካላቱ በጀትም ሆነ ሌሎች አስተዳደራዊ ነክ ነገሮችን ሲሠሩና በስፍራው ሲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን የጉዞና ተያያዥ ፈቃዶችን እንደሚያረጋግጥላቸው የጠቆሙት አቶ ደበበ ፥ በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከድርጅቶቹ ጋር በመቀናጀት ማረጋገጫ እንዲያገኙ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በየዕለቱ በረራ መፍቀድን ጨምሮ ኃላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን ፥ በዚህም 50 አጋር ድርጅቶች እስካሁን 509 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ ድጋፎችን እያጓጓዙ ይገኛሉም ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችም በየብስ ትራንስፖርት አማካኝነት መድረሳቸውን ጠቁመው ፥ ተገቢ ያልሆኑ ምክንያቶችን በመደርደር ‘‘ስርጭት አልተደረገም’’ የሚለው ቅሬታ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
መድኃኒቱ አቅርቦቱ እንዳለ ሆኖ መቀሌ ከገባ በኋላ ደግሞ ያስገባው አጋር አካል መድኃኒቱን የሚያጓጉዙበት ነዳጅ ያጣል ተብሎ አይታሰብም ያሉት አቶ ደበበ÷ አሸባሪው ህወሓት ከኮምቦልቻ የዘረፈው ነዳጅ በእራሱ ብዙ ነው።
በመሆኑም ‘‘ድጋፉን ለማጓጓዝ የነዳጅ ችግር ገጥሞናል’’ እየተባለ የሚነሳው ጉዳይም ውሃ አይቋጥርም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!