አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉሙሩክ ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ68 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ፡፡
ድጋፉም 70 ኩንታል ዱቄት፣ 75 ተሽከርካሪ የእንስሳት መኖ እና 60 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው በኮትሮባንድነት የተያዙ አልባሳትና ቁሳቁሶች ሲሆኑ፥ በክልሉ ለሚገኙ የጉጂ፣ ባሌ እና ቦረና ዞኖች በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ነው፡፡
የጉሙሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፥ ድጋፉ በክልሉ ድርቅ የደቀነውን ጉዳት ለመቀነስ እና የሕይወት አድኑን ሥራ ለማገዝ የተበረከተ ነው፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው፥ “ከሕዝብ የተሰበሰበን ሀብት ለህዝብ” የሚል መርህ ይዞ እየሠራ የሚገኘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሠ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ አብዱራህማን አብደላ፥ ድጋፉ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቁመው÷ በተለይም የእንሰሳት መኖው በአሁኑ ሰዓት ለከብቶቹ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉንም ከጉጂ እና ቦረና ዞን የመጡ አባገዳዎች እና የስራ ኃላፊዎች ተረክበዋል፡፡
በጎህ ንጉሡ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

