Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመከላከያ ሚኒስትሩና በኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር የተመራ ልዑክ የወንጪ ደንዲን ፕሮጀክት ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና በኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ የወንጪ ደንዲን ፕሮጀክት ጎበኘ።

በጉብኝቱም የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም ወቅት የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ የተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ገልፀው፥ አሁን በሙሉ አቅም ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

ክረምት ከመግባቱ በፊት የሚከናወኑ ተግባራትም በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀው፥ የቆረጣ ስራውም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል የመንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም እና ሁለት የሎጅ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመው፥ ሌሎቹ በግሉ ዘርፍ ይከናወናሉ ነው ያሉት።

ለፕሮጀክቱ መሳካትም ማህበረሰቡ አካባቢውን ተደራጅቶ በመጠበቅ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም በጉብኝቱ አካባቢው አሁን ላይ ሰላም መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በ4 ቢሊየን ብር ” ኢጃ ዴቬሎፕር ” የሚባል የልማት ድርጅት አቋቁሞ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የልማት ስራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት አካባቢም በዚህ የልማት ድርጅት አማካይነት ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትም በዚህ አካባቢ የተለያዩ ሎጆችን ገንብቶ ለግሉ ዘርፍ የሚያስተላልፍ መሆኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፕሮጀክቱን በማከናወን ላይ የሚገኘው የቻይና ኩባንያም ሌተቀን ስራውን በማከናወን ላይ መሆኑንም ተገልጿል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version