አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር ወጣቶች በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ማገልገላቸው ከሥራው ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን እያጠናከር መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ዮሐንስ አመነ እንደገለጹት÷ ከ21 ሺህ በላይ ወጣቶች በግብርና ሥራ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት፣ ትራንስፖርት ስምሪትና በሌሎችም መስኮች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የተለያዩ ክልሎች የሰላም ግንባታ ዘርፍ አስተባባሪዎችም ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልገሎት በሰላም ግንባታና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ማጠናከር ረገድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የካቢኔ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፒተር ኦይ÷ መከካበርና መቻቻል እንዲኖር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው÷ በክልሉ የሚገኙት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በክልሉ 3 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሥራ እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ናቸው፡፡ በመጀመሪው ዙር 1 ሺህ 200 ወጣቶች በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንድ ዓመት ሲሳተፉ ቆይተው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።
በተለያዩ ችግሮች መርሃ ግብሩ እየተፈተነ ቢሆንም ፈተናዎችን በማለፍ ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠርና የ2063ቱን የልማት ግብ ለማሳካት እንደሚሰሩም ዶክተር ዮሐንስ አመነ ገልጸዋል። በወጣቶቹ የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ ብሔራዊ አገልግሎት ለማሳደግ ግብ መቀመጡን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

