አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአድዋን ድል የሚዘክር አውደ-ርዕይ ለሕዝብ ተከፈተ።
አውደ-ርዕዩ ከዛሬ የካቲት 21 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይሆናል ተብሏል።
በአውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአድዋ ለአገር ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ እንደሚዘከር የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ተናግረዋል።
በአውደ-ርዕዩ ላይ የአድዋን ጀግኖችን የሚዘክሩ ስዕሎች፣ ፎቶግራፎችና የተለያዩ ተጨባጭ ታሪካዊ ቅርሶች በስፋት እንደሚቀርቡም ነው የገለጹት።
እነዚህ ስዕሎችና ፎቶግራፎች ወጣቱ ትውልድ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ እንዴት እንደቆመችና የድሉንም ትክክለኛ መረጃ ለማወቅ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ይህም ኅብረተሰቡ የአድዋን ድል በተመለከተ ያለውን መረጃ ለማስፋት እንደሚጠቅም ገልጸው፥ በዘርፉ ጥናት ለሚያድርጉ አካላትም ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአድዋ ድልን በተመለከተ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችና ትርክቶችን በትክክለኛ መረጃ ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረትም እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
ይህንንም ከግንዛቤ በመውሰድ ኅብረተሰቡ በአውደ-ርዕዩ በመሳተፍ የአገሩን ታሪክና ባህል በመጎበኘት የታላቁን አድዋ በዓል እየተዝናና እንዲዘክር ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋራ በጋራ በመሆን አውደ-ርዕዩን እንዳዘጋጁት ኢዜአ ዘግቧል።
የዘንድሮው 126ኛው የአድዋ የድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ከዛሬ ጀምሮ መከበር ጀምሯል ነው የተባለው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

