Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሴቶችን በሁሉም ረገድ የማብቃቱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረው የሴቶች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል ተከብራል፡፡
 
በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ሴቶች እርስ በርስ እንደጋገፍ ፣እንረዳዳ፣ አንድነታችንን አጽንተን በጋራ እንቁም፣ ያኔ ችግሮቻችንን በምንፈልገው ፍጥነት እየቀረፍን እንሄዳለን ብለዋል፡፡
 
የሀገርን ሁለንተናዊ ሠላምና አንድነት መጠበቅ ላይ ሴቶች እያበረከታችሁት ያለው አስተዋጽኦ ቀደምት ሴቶች ሲያደርጉ እንደነበረው ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
 
ሀገሪቱ የሕልውና ፈተና ወቅት በገባችበት ጊዜ ለጀግናው ሠራዊት የኋላ ደጀን በመሆንም በግንባርም በመሠለፍ ሀገር አስቀጥላችኋል፤ ለዚሕም ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች ነው ያሉት።
 
ከንቲባ አዳነች ከከተማው ካቢኔ 32 በመቶ ሴቶች እንዲታቀፉ ማድረግ መቻሉን አውስተው÷ይህንንም ሴቶችን በሁሉም ረገድ የማብቃት እንቅስቃሴ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ብለዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ÷ሴቶች በሁሉም ረገድ ተወዳዳሪነታችንን በማሳደግ ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ሰላምና ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
 
የከተማ አስተዳደሩ ሴቶችን ወደ ተሳትፎ ለማምጣት ብሎም በእኩልነት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን፣ በህዝብ እንደራሴ በሚገባ እንዲወከሉ በማድረግ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
 
በመርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌደራል መንግሥት መዋቅር በኃላፊነት የሚያገለግሉ ሴቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ የሙያ መስክ ተጽዕኖ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሳደሩ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡
 
በዚህም በተለያዩ ዘርፎች ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ እንስቶች ሴቶች እንደሚችሉ ከሕይወት ልምዳቸው በዋቢነት ምሳሌዎችን በማቅረብ ተሳታፊዎችን ማነቃቃታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version