አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ የማብቃቱን ተግባር ለማጠናከር የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ፡፡
ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ፥ በአገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶች ቀን ( ማርች 8) ዛሬ በጃፓን ኤምባሲ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ“ በሚል መሪ ቃል አክብሯል፡፡
በመድረኩ የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና የተለያዩ አምባሳደሮች ተገኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን የማረጋገጥና ሴቶችን በማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የማብቃት ስራን አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተናገሩት፡፡
የጾታ እኩልነትና ሴቶችን በሁሉም መስክ የማብቃት ስራ መንግስት በተናጥል የሚያከናውነው ተግባር ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ÷ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ መጠቆማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ህጻናት ሁለንተናዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ በዘላቂነት ከችግር እንዲወጡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የጃፓን ኤምባሲ በኢትዮጵያ አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶችን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መድሎን ማስቆም የሚቻለው በሁሉም አካላት በኩል ያልተቋረጠ ጥረትና ርብርብ ማድረግ ሲቻል መሆኑን አንስተዋል፡፡
መድረኩ የአብሮነትን እሴት ለማዳበርና የሴቶችን አዎንታዊ አቅም ለማጎልብት እንዲቻል የመረጃ፣ የልምድ ልውውጥ የሚፈጥር መሆኑንና በቀጣይነትም የቅንጅታዊ ስራዎችን ለማጎልበት እንዲቻል የተሳበ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

