Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ ሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ ጥፋተኛ በተባሉ ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣የካቲት 29፣2014(ኤፍ ቢሲ) ከሰኔ 15 ክስተት ጋር ተያይዞ ከሕዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ሲታይ በቆዩና ጥፋተኛ በተባሉ 31 ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ጥፋተኛ በተባሉ 31 ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ችሎቱ በእያንዳንዳቸው ተከሳሾች ላይ ከእድሜ ልክ እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ ነው ያስተላለፈው፡፡
ከቅጣት ውሳኔው በፊት በተከሳሾች የቀረበውን የቅጣት ማቅለያ ተቀብሎ የመረመረው ችሎቱ ለአራት ተከሳሾች አምስት ማቅለያዎችን፣ ለ20 ተከሳሾች አራት ማቅለያዎችን፣ ለአራት ተከሳሾች ሦስት ማቅለያዎችን እና ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ የቆዩ ሦስት ተከሳሾችን ደግሞ አንድ ማቅለያ ተቀብሏል፡፡
ማኅበራዊ አገልግሎት፣ የቤተሰብ ኀላፊነት፣ ሕመም፣ ወንጀሉን ከመፈጸማቸው በፊት የነበራቸው ለሀገር የተከፈለ ዋጋ እና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መኾኑ በቅጣት ማቅለያነት የተያዙ ናቸው፡፡
ችሎቱ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ የቆየውን የሻምበል መማር ጌትነት፣ በላይሰው ሰፊነው እና ልቅናው ይሁኔ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ሌሎች 18 ተከሳሾች በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች በ15 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች 16 ዓመት፣ አራት ተከሳሾች በ18 ዓመት እና ሁለት ተከሳሾች በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version