Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሁዋዌ ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የ5ጂ አገልግሎት ለማዳረስ የሚሠሩ ኩባንያዎችን እንደሚደግፍ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁዋዌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የኔትወርክ አገልግሎት ሠጪዎች እና አጋሮች ጋር ኃይል ቆጣቢ እና ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እውን ለማድረግ እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

ሁዋዌ ይህን ያስታወቀው በዚህ ዓመት ጎልቶ በወጣበት ከፈረንጆቹ የካቲት 28 እስከ መጋቢት 3 በባርሴሎና ሲካሄድ በቆየው “ዓለምአቀፍ የሞባይል አውደ ርዕይ” ላይ ነው፡፡

ኩባንያው በቀጣይ የአምሥተኛውን ትውልድ “5 ጂ” ኔትወርክ ዝርጋታ በበርካታ ሀገራት ለማዳረስና ቀላል፣ ከአካባቢ ብክለት ነጻ እና እጅግ ዘመናዊ የመረጃ እና ኮሙኒኬሽን መሠረተ-ልማት ዝርጋታዎች ላይም ትኩረት አድርጎ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ነው በመረጃው ያመላከተው፡፡

ሁዋዌ እስካሁን ድረስ በስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ፊንላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ከ13 ሀገራት በላይ ያሉ ደንበኞቹን በ”5ጂ” መሥመር ዝርጋታ መድረስ የቻለ ሲሆን፥ የደኅንነትና ብቃት ማረጋገጫም ከሀገራቱ አግኝቷል ነው የተባለው፡፡

በቀጣይም የ5ኛውን ትውልድ የኔትወርክ አገልግሎት ጨምሮ የተለያዩ የኩባንያውን አገልግሎቶች ለማቅረብ ከተለያዩ ሀገራት የኔትወርክ አገልግሎት ሠጪ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ጋር ከ3ሺህ በላይ ሥምምነቶችን መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡

ሁዋዌ በባርሴሎና በተካሄደው “ዓለም አቀፉ የሞባይል ዓውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ ዘመናዊና ከፍተኛ መረጃዎችን የመሸከም አቅም ያላቸው የሞባይል ቀፎ ምርቶች፣ ታብሌት ኮምፒውተሮች እና በቀጣይ ሊሰጣቸው የተዘጋጀባቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች ለደንበኞቹ እና ለአዳዲስ ተጠቃሚዎች ይፋ አድርጓል፡፡

ሶኒ፣ አፖ፣ ቲሲኦ እና ሳምሰንግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ኩባንያዎችም ዘመናዊ የሥልክ ምርቶቻቸውን በዋናነት በዓውደ-ርዕዩ ላይ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version