Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለድርቅ እና ግጭት ተጋላጭ የሆኑ አካላትን በጥናት በመለየት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ድርቅና ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በጥናት በመለየት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አካላት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የማኅበሩ የቦርድና ከፍተኛ አመራሮች በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ተመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታአ በወቅቱ እንደገለጹት÷ ማኅበሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ድርቅና ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በጥናት በመለየት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ አካላትን እየረዳ ነው፡፡
በዚህም በሁለቱ የባሌ ዞኖች ለሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ለድርቅ ከተጋለጡ ከ1 ሺህ 150 ለሚበልጡ አባወራዎች በአንደኛው ዙር ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው 340 ኩንታል ዱቄትና 2 ሺህ ሊትር ዘይት ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር ደግሞ በዞኑ ለጎሮ ወረዳ ድርቅ ተጎጂዎች ከዓይነት ድጋፍ ይልቅ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም ተጎጂዎቹ በራሳቸው የሚፈልጉትን ገዝተው ለመጠቀም ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ለ500 አባወራዎች ለእያንዳንዳቸው 4 ሺህ ብር ለማስተላለፍ የሚያስችል የተጠቃሚዎች የባንክ ሂሳብ ቁጥር እየተከፈተላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው÷ እስካሁን 300 የሚሆኑ ሰዎች የባንክ ሂሳብ የከተከፈተላቸው ሲሆን በዚህ ሳምንት ለተቀሩት በመክፈት ገንዘቡ ይተላለፍላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ድጋፉ በገንዘብ መሆኑና በቀጥታ በተጎጂዎቹ የባንክ ሂሳብ ላይ ገቢ መደረጉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረትና የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ ሁነኛ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

በማኅበሩ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ጀማል አባቦራ÷ በክልሉ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የዕለት ድጋፍና በቋሚነት እንዲቋቋሙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የድርቅ ተጎጂዎቹ በበኩላቸው÷ የባንክ ሂሳብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየተከፈተላቸው መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይ ከድርቁ አገግመው የተረጋጋ ኑሮ ለመምራት እንዲችሉ መንግስት የምርጥ ዘርና ሌሎች ዘላቂ ድጋፎችን እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version