አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ ፍጹም ነጻና አሳታፊ በመሆን ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እድገት መሰረት የጣለ መሆኑን የጉባዔው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ሲሆን÷ ጉባዔው ትናንት ባካሄደው ውሎ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም እንዲሁም የፓርቲውን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች መርጧል፡፡
በተጨማሪ ጉባዔው የፓርቲውን የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የቁጥጥርና ኤንስፔክሽን ኮሚሽን ሪፖርት አድምጦ አጽድቋል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች የጉባዔው ተሳታፊዎች ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሃሳባቸውን በመግለጽ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ጉባዔው ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ የፓርቲው አባላት እንደ ቀድሞው የኢህአዴግ ዘመን የዳር ተመልካች ሳይሆኑ እኩል ተሳታፊና የአመራር ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከብልፅግና ፓርቲ ሐረሪ ጽ/ቤት የመጡትና የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ነቢል መኸዲ፤ በጉባዔው ቀድሞ አጋር ተብለው ተመልካች ብቻ የነበሩ ፓርቲዎች አሁን ላይ በአገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው ፍጹም ዴሞክራሲያዊ የሆነና አሳታፊ ምህዳር የተፈጠረበት መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እድገት ጠንካራ መሰረት የሚጥል ነውም ብለዋል፡፡
ከብልጽግና ፓርቲ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ጽ/ቤት የመጡትና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አበራሽ ደቻስ በበኩላቸው፥ በጉባዔው ላይ የታየው አሳታፊነት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታና ብልጽግና እውን እንደሚሆን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጀማል ረዲ ÷ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት እኩል እየተሳተፉ በመሆናቸው ጉባዔውን ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ የገዢ ፓርቲ ጉባዔዎች ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

