አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ፣ እንግልቱ እና የህገ ወጦች መበራከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ለማውጣትና ለማደስ እንዲሁም የልደት፣ የሞትና የጋብቻ ሰርተፍኬት ለማግኘት ችግሮች መኖራቸውን ኢዜአ ቅኝት ባደረገባቸው አካባቢዎች አረጋግጧል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አገልግሎት ፈልጎ ከሚሰለፈው በተጓዳኝ “ጉዳይ እናስፈፅማለን” የሚሉ ህገ ወጦች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የአገልገሎት ማግኛ ሳይሆን ከፍተኛ የእንግልት ስፍራ ሆኗል ይላሉ ነዋሪዎቹ።
መታወቂያ ወይም የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ጉዳይ “አገልጋይ የሌለበት፣ ለህገ ወጥ ደላሎች ገበያ፤ ለተገልጋዮች ደግሞ የእንግልትና ምሬት ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል።
የወረዳ 6 ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ጠጅቱ ደገፋ÷ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ላይ የተፈጠረው ችግር ከወረዳው አቅም በላይ ሆኗል ይላሉ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን በማስታወስ÷ አዲስ የመኖሪያ መታወቂያ መስጠት አዋጁ ከደነገጋቸው ክልከላዎች መካከል መሆኑን ጠቁመው÷ ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት ከየካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ አገልገሎቱን ለመስጠት ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በበኩሉ÷ በአገልገሎት መስጫ ቴክኖሎጂው ላይ የኔትወርክ መሰረተ ልማት መቋረጥ በማጋጠሙ ችግሩ ተከስቷል ብሏል።
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር መላከ መኮንን የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ቀደም ሲል በማንዋል ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው÷ አሰራሩን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ ታስቦ “ወረዳ ኔት” በተሰኘ ቴክኖሎጂ አገልገሎቱ መጀመሩን ተናግረዋል።
ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከሚመለከታቸው አካላት የኔትዎርክ መሰረተ ልማት ከማስተካከል ጎን ለጎን የተሻለ አቅም ያለውና የቀጥታ ዳታ ማዕከል የኔትዎርክ መሰረተ ልማት የማልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የተፈጠረው ችግር እስኪፈታ በጊዜያዊነት በማንዋል እንዲሰራ እየተደረገ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ÷ ከአገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር አንፃር በቂ ምላሽ አለመሰጠቱን አምነዋል።
በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አጋጣሚውን ተጠቅመው ችግር እየፈጠሩ ያሉ ህገ ወጥ ደላሎችን ለመቆጣጠር ኤጀንሲው ከጸጥታ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ በዚህም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ አንድ እና ሁለት በሚባሉ አካባቢዎች 7 ህገ ወጥ ደላሎች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የገለጹት፡፡
ኤጀንሲው ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እየጠየቀ ቴክኖሎጂው ዳግም ስራ እስከሚጀምር ተገልጋዮች ባለው የማንዋል አገልግሎት አማራጭ እየተገለገሉ በትእግስት እንዲጠባበቁም ነው አቶ መላክ የጠየቁት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

