Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚያዘምኑ ሁለት ስምምነቶች ተፈረሙ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 5፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያሳልጡና የሚያዘምኑ ሁለት ስምምነቶችን በዛሬው ዕለት ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ተፈራርሟል፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ በዛሬው እለት የተፈረመው ውል ስምምነት የመጀመሪያው ለከተማው የሚመጥኑ ዘመናዊና ለአገልግሎት ተስማሚ የሆኑ 110 ባሶችን ከቻይናው ዩቶንግ ባስ ኩባንያ ጋር ከ15 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግዥ ለመፈፀም ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ኩባንያው ባሶቹን በ8 ወራት ውስጥ የሚያቀርብ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ሁለተኛው ስምምነት ደግሞ የአንበሳ አውቶብስን አቅም የሚያዘምነውና የሚያሳድገው በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን የታገዘው የብልህ ትራንስፖርት ስርዓት ከቻይናው ሺንዶ ሂሰንስ ትራንስ ቴክ ኩባንያ ጋር የተፈፀመ ውል ነው፡፡

ይህም ውል ከ14 ሚሊየን ዶላር በላይ እና በሃገር ውስጥ በተጨማሪ 9 ሚሊየን ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን÷ አጠቃላይ ድርጅቱን አለም ከደረሰበት የትራንስፖርት መሰረተ ልማት እድገት ጋር የሚያቀራርብና ከወረቀት ነፃ የሆነ አገልግሎት እንዲሁም ለደንበኞች በየተርሚናሉና የጉዞ ዲጂታል መረጃ አቀረርቦትም እንዲኖር የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

በስምምነቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ለከተማ ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች ኪራይ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደጉም ገልፀው የትራንስፖርት አገልግሎትን መንግስት ብቻውን የሚፈታው አይደለም ፤የግሉ ሴክተር አስተዋፅኦ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እነዚህ ስምምነቶች የእውቀት ሽግግር እና ዘመናዊነትን አለም የደረሰበትን ቀልጣፋ የአይሲቲ አገልግሎትን ያካተተ መሰረታዊ የትራንስፖርት የለውጥ ስራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ስምምነቱን ከተማውን አስተዳደሩን በመወከል የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ተፈራርመዋል፡፡

 

Exit mobile version