አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ጦር በዩክሬን እያካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የምትገኘውን የኬርሰንን ክልል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ኢጎር ኮናሼንኮቭ እንዳሉት፥ የዶኔስክ ህዝቦች ወታደሮች የማጥቃት ዘመቻቸውን አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን የዩክሬንን ፀረ – ማጥቃት ሰብረው በመግባት በኬርሰን ክልል ውስጥ የምትገኘዋን ፓንቴሎሞኖቫካን መቆጣጠራቸውን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የዩክሬን የውጭ ወታደሮችን ምሽግ መቆጣጠሩን እና 10 አሜሪካ – ሰራሽ የጃቬሊን ፀረ ታንክ ሚሳኤል መያዙን ገልፀዋል።
በሩሲያ ኃይሎች የተያዙት ሁሉም የውጭ ጦር መሳሪያዎች ለሉሃንስክ እና ዶኔስክ ህዝቦች ህዝባዊ ሃይሎች እየተላለፉ መሆኑንም አስረድተዋል።
ባለፉት ቀናት በተካሄደው ዘመቻ የሩሲያ አየር ኃይል በተመረጡ 16 ኢላማዎች ላይ የተሳካ ያሉትን ድብደባ መካሄዱን ገልጸው፥ የዩክሬንን ሱ -24 እና ሱ-25፣13 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዲሁም አንድ ሚግ 8 አውሮፐላን መመታታቸውን ተናግረዋል፡፡
ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ የሩሲያ ጦር በድምሩ 156 ሰው- አልባ አውሮፕላኖች፣ 1 ሺህ 306 ታንኮች እና ሌሎች የጦር ተሽከርካሪዎችን፣ 127 ሮኬቶች፣ 471 የመስክ መድፍ ጠመንጃዎች እና ሞርታሮች ማውደሙንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡
በሌላ በኩል የሩስያ አየር ኃይል በዛሬው ዕለት ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሰ የዩክሬን ዋና ከተማ በሆነችው ኪየቭ የአየር ድብድባ ያካሄደ ሲሆን፥ በመዲናዋ በሚገኘው አንድ ግዙፍ ህንፃ ላይ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተጠቅሷል።
የሩሲያ ባለስልጣናት 20 ቀናትን ያስቆጠረው ወታደራዊ ዘመቻ በተያዘለት መርሀ ግብር መሰረት እየተካሄደ ነው ሲሉ መናገራቸውን የዘገበው ስፑትኒክ ነው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!