አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳይ ተጠባባቂ ሚኒስትር ሌ/ጄኔራል አናን ሃሚድ ሞሃመድ ኦማር ጋር ተገናኝተው ኢትዮጵያውያን ከመኖረቲያ እና ከሥራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ በሱዳን እየገጠማቸው ያለውን ችግር ማቃለል በሚቻልበት ሁኔታ ተወያይተዋል።
የሱዳን መንግስት የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ አውጥተው በሕጋዊ መንገድ ይኖሩ ዘንድ ሲያሳስብ ቢቆይም÷ በሱዳን የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና ለመኖሪያም ሆነ ለሥራ ፈቃድ የሚያስፈልገውን ክፍያ መፈጸም የማይችሉ በመሆኑ ለችግር ተጋላጭ ሆነዋል።
የሱዳን መንግስት በስራ ላይ ያዋለው የመኖሪያ እና ሥራ ፈቃድ ክፍያ ከኢትዮጵያውያን የመክፈል አቅም በላይ በመሆኑ÷ አብዛኞቹ ሕጋዊ ሆኖ ለመኖር መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከሱዳን ወገን ልዩ ድጋፍ እና ትብብር እንዲደረግ አምባሳደር ይበልጣል ጠይቀዋል፡፡
ወደ አገራቸው በተሽከርካሪ መመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን አዲስ የተጣለው የመውጫ ቪዛ ክፍያ እንዲነሳ ቀደም ሲል ስራ ላይ የነበረውን ክፍያ በመፈፀም መውጣት እንዲችሉ፣ የመኖሪያ ፈቃድ በማውጣት ሕጋዊ ሆኖ መኖር ለሚሹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለቅጣት የሚጠየቀው ክፍያ እንዲነሳላቸው፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ለእንግልት እንዳይዳረጉ የመክፈል አቅማቸውን ባገናዘበ ሁኔታ የመመሪያውን አፈፃፀም በተመለከተ ለተወሰነ ጊዜ እንዲታገሱ ጠይቀዋል፡፡
ሌ/ጄኔራል አናን ሃሚድ ሞሃመድ ኦማር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸው ይህንን ግንኙነት ለማጠናከርም መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የመተማ/ጋላባት የድንበር ኬላ መከፈቱ አወንታዊ ዕርምጃ መሆኑን እና መ/ቤታቸው የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች እና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለማሳለጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን የሚገጥሟቸውን ችግሮች እንደሚረዱ ገልፀው÷ከመውጫ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ ክፍያ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ መዋጋት እና በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ የትብብር መድረኮችን እንደገና ማንቀሳቀስ እንደሚገባም ሌ/ጄኔራል አናን ሀሚድ ሞሀመድ ኦማር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

