Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሚቀጥሉት 3 ወራት 150 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል- አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 3 ወራት 150 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት መግለጫ÷ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አማካይነት በየወሩ 50 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ገበያውን ለማረጋጋት በአጭር ቀናት ውስጥ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ቤት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 8 ሚሊየኑ በባቡር ተጓጉዞ መግባቱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ አቅጣጫ ከተቀመጠባቸው ጉዳዮች መካከል የዋጋ ንረትን በቶሎ በማረጋጋት የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በዘይት አቅርቦት ላይ እየተሰራ ያለው ስራ የውሳኔው አካል እንደሆነ በመግለጫቸው አንስተዋል ።

የዘይትን አቅርቦት እና ዋጋ ለማሻሻል ከውጭ ከሚገባው በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ለአምራቾች ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ከውጭ ድፍድፍ ዘይት አስገብተው ለሚያጣሩት ለፊቤላ ፣ ሸሙ እና ሀማሬሳ ፋብሪካዎች መንግስት የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ዘይት ለሚያመርቱ አነስተኛ ፋብሪካዎችም ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ያስታወቁት።
ከዚህ በተጨማሪ በሚቀጥለው ዓመት በሚከፈል የኤሊሲ ስርዓት ዘይት ለሚናስገቡ ኩባንያዎች ፈቃድ መሰጠቱንም ጠቁመዋል ።

መንግስት ከውጭ ከማስገባት ባለፈ የምግብ ዘይትን ሙሉ በሙሉ ከታክስ ነፃ ማድረጉን ገልፀው፥ በዚህም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 23 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መንግስት አጥቷል ብለዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ መንግስት ለነዳጅ 100 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉም ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባች ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በፍራንኮቫሉታ የገባ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ።

በዓልአዛር ታደለ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version