አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የተዘጋጀው ኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር፣ ወዳጅ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እርዳታ እንዳይሰጡ የሚያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ሊቀመንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተረፈ ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ረቂቅ ህጉ ቢጸድቅ ዳያስፖራዎች በሀገራቸው ልማት እንዳይሳተፉ፣ ገንዘብ ወደ ሀገራቸው እንዳይልኩና ኢትዮጵያ ከገቡም እንዳይመለሱ የሚከለክል፣ ረጂ ተቋማትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያቆሙ የሚያስገድድ ነው።
ከኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ ጋር አብሮ የሚመከርበት ተመሳሳይነት ያለው ኤስ አር 3199 የተባለ ረቂቅ ሰነድ በሴኔት በኩል እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው÷ በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን እጅ የመጠምዘዝ ሙከራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው በሚችሉት አማራጮች ሁሉ ረቂቅ ህጉ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቢሮ እንዳይደርስ ማድረግ አለብን የሚሉት ደግሞ÷ በምክር ቤቱ የሶሻል ሚዲያና ዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያን ዳይሬክተር አቶ ስዩም ሀብተወልድ ናቸው።
ምክር ቤቱ ለበርካታ የኮንግረስ አባላት ረቂቅ ህጉ ላይ ድምጽ እንዳይሰጡ የሚጠይቅ ደብዳቤ መላካቸውንም ጠቁመዋል።
ረቂቅ ህጉ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ለረጅም ዓመታት የሚቆይ፣ የኢትዮጵያም ሆነ የአሜሪካ መንግስት ቢቀያየር ለማንሳት የሚያስቸግር በመሆኑ አሁኑኑ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንም በሚችሉት ሁሉ በመረባረብ ለኮንግረስና ሴኔት አባላት ስልክ በመደወል፣ የተቃውሞ ፊርማውን በመፈረም ረቂቅ ህጉን ማምከን ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
በትእግስት ስለሺ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

