አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋሞ ዞን አርሶ አደሮች በሕገ-ወጥ ደላሎች ምክንያት የገበያ ችግር አጋጥሞናል፥ የድካማችንንም ዋጋ አጥተናል ሲሉ ተናገሩ፡፡
አርሶ አደሮቹ አንድ ኪሎ ሙዝ 8 ብር እየሸጡ÷ ምንም እሴት ያልጨመሩ ደላሎች ግን ከ21 ብር በላይ እየሸጡ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡
በእንዲህ ዓይነት የገበያ ሁኔታ የተማረሩት አርሶ አደሮች÷ በምናመርተው ሙዝ ዋጋውን የመተመን መብት እንኳን የለንም ሲሉ በስፍራው ለተገኘው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጋዜጠኞች ቡድን ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
በግብይቱ ውስጥ የሕገ-ወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች እጅ በመርዘሙ÷ የድካማቸው ዋጋ በሌሎች እንዲወሰድ እና ሸማቹ ህብረተሰብም በውድ እንዲገዛና የዋጋ ንረት እንዲገጥመው ማድረጉንም ነው አርሶ አደሮቹ የተናገሩት፡፡
የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቲቆ ቲላንቴ ሰለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የችግሩን መኖር አምነው÷ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም መፍትሄ ሊገኝ አለመቻሉን ነው የገለጹት።
የዋጋ ንረትን ከሚጨምሩ፥ የኑሮ ውድነትንና የህብረተሰቡን ችግሮች ከሚያባብሱ ጉዳዮች አንዱ የሕገ-ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት መሆኑን በመጠቆም÷ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱና እንዳይስፋፉ መንግስት በሕገ-ወጥ ደላሎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይመክራሉ፡፡
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሲሳይ ሙላቴ÷ ችግሩ በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ጠቅሰው÷ ጉዳቱ ደግሞ ለአምራቹና ለሸማቹ፥ አለፍ ሲልም ለሀገር መሆኑን አንስተው መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የችግሩ ዋናኛ ምክንያትም የስግብግብ ደላሎች ህገወጥ ተግባር፣ የአርሶ አደሮች ግንዛቤ አለማደግ እና የገበያ ስርዓቱ አለመዘመንና የግብይት ሰንሰለት መርዘም መሆኑን ጠቅሰው፥ የገበያ ስርዓቱን በአግባቡ በመምራት አርሶ አደሩንም፥ ሸማቹንም ተጠቃሚ ማድረግ መቻል አለበት ብለዋል፡፡
ችግሩ የፖሊሲ ሳይሆን የአተገባበር በመሆኑ መንግሥት ተግባራዊ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

