Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዓለም ጤና ድርጅት ፈቃድ ቢሰጠውም ወደ ትግራይ ያጓጓዘው እርዳታ አለመኖሩ ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት 95 ሜትሪክ ቶን መድሃኒትና የመድሃኒት ግብዓቶችን ወደትግራይ እንዲያጓጉዝ ፈቃድ ቢሰጠውም እስካሁን የመድኃኒት ግብዓቱን ሟጓጓዝ አለመጀመሩን ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኘ መረጃ አመላከተ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም መድኃኒቶችን ወደትግራይ ክልል እንዳናስገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ከለከለን በሚል በተደጋጋሚ ክስ ቢያቀርቡም÷ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንደገለጹት የዓለም ጤና ድርጅት የመድሃኒት ግብአቶቹን እንዳያጓጉዝ የከለከለው አካል የለም፡፡
በዚህም ቀድሞ ፈቃድ እንደተሰጣቸው እየታወቀ ክልከላ ተደርጎብናል በሚል የሚቀርበው ክስ መሠረተ ቢስ ነው ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ጤና ድርጅት የመድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዲያጓጉዝ በፈረንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 14 ቀን በጤና ሚኒስቴር ፈቃድ እንደተሰጠውም ተመላክቷል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ በጤና ሚኒስቴር ስለተሰጠው ፈቃድ አመስግኖ÷ መጋቢት 15 ቀን 2022 ዓ.ም ለብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ከመጋቢት 21 ቀን 2022 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2022 ዓ.ም የመድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንደሚያጓጉዝ አስታውቋል፡፡
ይሁንና የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከኢትዮጵያ ወኪላቸው በተቃራኒ መጋቢት 17 ቀን 2022 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ የመድሃኒት አቅርቦት እንዳይገባ ከልክሏል ሲሉ በሀሰት ወንጅለዋል፡፡
ኢፕድ ይህንን ጉዳይ ለማጣራት የዓለም ጤና ድርጅት የአዲስ አበባ ወኪልንና የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የስራ አመራሮችን ያነጋገረ ሲሆን÷ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ እንደገለጹት ድርጅቱ ፈረንጆቹ መጋቢት 21 ቀን 2022 ጀምሮ ላለፉት ሁለት ቀናት ምንም አይነት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳላጓጓዘ አረጋግጠዋል፡፡
በተመሳሳይ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ የኮሙኒኬሽ ክፍል÷ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመሆን በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ከፈረንጆቹ መጋቢት 14 ቀን 2022 ጀምሮ ፈቃድ የሰጣቸውና ድርጅቱ ከመጋቢት 21 ቀን 2022 ጀምሮ እንደሚያጓጉዝ የገለጸ ቢሆንም÷ ባለፉት ሁለት ቀናት ወደ ትግራይ የላከው እርዳታ አለመኖሩን ምንጫችን አረጋግጧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version