Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህወሓት ወደ ክልሉ የሚገባውን እርዳታ ለጦርነት ማዋሉ አልበቃ ብሎት ከገበሬ እህል እየቀማ ይገኛል – የትግራይ ወጣቶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ወደ ትግራይ የሚገባውን የእርዳታ ምግብ ታጣቂ ሀይሉን እየቀለበበትና የተረፈውን ለነጋዴዎች እየሸጠ የትግራይን ሕዝብ በረሃብ እየቀጣ ይገኛል ሲሉ የቡድኑን ግፍ በመሸሽ ወደ አማራ ክልል የገቡ የትግራይ ወጣቶች ገለጹ።

ኢፕድ ያነጋገራቸው ወጣቶች የእርዳታ ምግብና መድኃኒቶች በአውሮፕላንና በመኪና ወደ ትግራይ እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው ፥ የሚገባው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከመስጠት ይልቅ ለግለሰብ ድርጅቶች እየተሸጡና ታጣቂ ሀይሉን እየቀለበበት መሆኑን አስረድተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ በነበረበት ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ወደ ክልሉ በሚገባ እርዳታ ተጠቃሚ ነበር የሚለው ከአዲግራት ከተማ ተፈናቅሎ ወደ አማራ ክልል የገባው መሓሪ አብራሓ ፥ አሁን ግን እንኳን እርዳታ ሊሰጥ ይቅርና ሕዝቡ እህልና ገንዘብ አምጣ እየተባለ በህወሓት የሽብር ቡድን ግፍና መከራ እየደረሰበት ይገኛል ብሏል።

“አውሮፕላን የእርዳታ ቁሳቁስ ይዞ በቀን ሁለት ጊዜ ወደ ትግራይ ይመላለሳል፤ መኪኖች በአፋር በኩል ብዙ የእርዳታ ምግብ ጭነው ወደ ትግራይ ገብተዋል” የሚለው ወጣት መሓሪ ፥ ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ እነዚህን የእርዳታ ምግብና መድኃኒት የት እንደሚገቡ እንደማያውቅ ገልጿል።

በሕዝብ የጤና ተቋማት መድኃኒት የሚባል ነገር እንደሌለና በእርዳታ የሚገቡ መድኃኒቶችና የሕክምና ቁሳቁሶች ለግል መድኃኒት ቤቶች እየተሸጡ መሆኑንም ተናግሯል።

በዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም መሪነት የዓለም መንግሥታት የእርዳታ ምግብና መድኃኒት ወደ ትግራይ ክልል እየገባ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው የሚለው ወጣት መሓሪ ፥ ከመናገራቸው በፊት ወደ ክልሉ የሚገቡ የእርዳታ ምግብና መድኃኒቶች የት እየገቡ ነው ብለው መጠየቅ አለባቸው ሲልም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሚዛናዊነት የጎደለው ወቀሳ ኮንኗል።

የትግራይን ሕዝብ በረሃብ እየጨረሰ ያለው የህወሓት የጥፋት ቡድን መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

“የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ያለውን በጎ አመለካከት በትክክል እያየነው ነው፤ ከትግራይ ተሰዶ የሚመጣውን ሕዝብ እየተንከባከበ ያለው በሕወሓት እንደ ጠላት የሚታየው የአማራ ሕዝብ ነው” ብሏል።

በሚኖርበት አካባቢ ከሦስት ጊዜ በላይ ለእርዳታ ተመዝግቦ አንድ ጊዜም እንዳላገኘ የሚናገረው ደግሞ የአዲ ጉዶም ከተማ ነዋሪው ቢንያም አርአያ ነው።

እሱ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ህዝብ እርዳታ እንደማያገኝ የገለጸው ቢንያም ፥ “ወደ ትግራይ የሚገባው እርዳታ ወደ የት ነው የሚሄደው የሚለውን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው” ሲልም ተናግሯል።

መኪኖችና አውሮፕላኖች የእርዳታ መድኃኒትና ምግብ ይዘው ወደ ክልሉ እንደሚገቡ ገልጾ ፥ የትግራይ ሕዝብ የዚህ እርዳታ ተጠቃሚ አለመሆኑን ጠቁሟል።

ህወሓት ወደ ክልሉ የሚገባውን እርዳታ ለጦርነት ማዋሉ አልበቃ ብሎት ከገበሬ እህል እየቀማ ይገኛል የምትለው ደግሞ የአዲግራት ከተማ ነዋሪዋና ለቤተሰቦቿ ደህንነት ሲባል ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ወጣት ናት።

ሀገርና ሕዝብን የሚጠብቅ መከላከያ ሠራዊትን የከዳ ጨካኝ ቡድን ከዚህም በላይ ቢያደርግ አይገርምም ስትል የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ደረጃ አስረድታለች።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version