Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዩክሬን ቀውስ የባይደን አስተዳደርን ተጨባጭ የአመራር ድክመት ያሳበቀ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬን ቀውስ የባይደን አስተዳደር ተጨባጭ የአመራር ድክመት እንዳለበት ያሳበቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡

አሜሪካ እንደ ዓለም ኃያል ሀገር በችግር ፈቺነት፣ በመፍትሄ አመላካችነት ፣ በመሪነት እና በወታደራዊ መሳሪያ አቅርቦት ልቃ ከመውጣት ይልቅ ከትንንሽ ሀገራት የድጋፍ ጥያቄ መሻቷ እና አንሳ መታየቷ ትዝብት ላይ እንደጣላት ተመለከተ፡፡

የባይደን አስተዳደርም በዩክሬን ቀውስ “የዓለም ኃያል ሀገር” የሚለው ትርጉም የጠፋበት እና ተጨባጭ የአመራር ድክመት እንዳለበት ያሳበቀበት ክስተት ሆኗበታልም ነው የተባለው፡፡

በአሜሪካ ተሥፋ ያደረገችው ዩክሬን ÷ ተሥፋዋን ውሃ በልቶት ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ እየገባች እንደምትገኝ ቲ አር ቲ ወርልድ ዘግቧል፡፡

በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ እንደነበረው አሜሪካ፥ ቱርክን ሩሲያ ሠራሽ ኤስ 400 የተሰኘ የሚሳኤል መቃወሚያዋን ለዩክሬን እንድትልክ በጎን ስታግባባ ሰንብታለች፡፡

አሜሪካ እንዲህ ዓይነት የማግባቢያ ሥራ ሥትሠራ የመጀመሪያዋ እንዳልሆነና ቀደም ብሎም ፖላንድ ሚግ 23 ተዋጊ ጀቷን ለዩክሬን እንድታስተላልፍ የማሳመን ሥራ ሥትሠራ እንደነበር ይታወሳል፤ በወቅቱ ፖላንድ በማስተላለፍ ሂደቱ ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ እንደማትፈልግ ቁርጥ አድርጋ ገልጻ ጉዳዩ በዚያው ተቋጭቷል፡፡

ከዚህ በኋላም አሜሪካ የሩሲያ ዓየር መቃወሚያ ያላቸውን የኔቶ አባል ሀገራት መቃወሚያቸውን ለዩክሬን እንዲያስተላልፉ ጠይቃለች፡፡

ግሪክ ሩሲያ ሠራሽ ዓየር መቃወሚያዎች እንዳሏት ባትደብቅም ከአሜሪካ የተነሳውን የተባበሩኝ ጥያቄ ግን በፍጥነት ነው ውድቅ ያደረገችው ተብሏል፡፡

በዚህ ወር መጀመሪያም የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዌንዲ ሸርማን ቱርክን እንደጎበኙ የተጠቆመ ቢሆንም፥ ከዚህ ቀደም አሜሪካ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ የሀገራቱን ትብብር ከጠየቀችው በዘለለ ቱርክን ሩሲያ ሰራሹን የሚሳኤል መቃወሚያዋን ለዩክሬን እንድትልክ የሚጠይቅ ምንም ዓይነት ይፋዊ ሃሳብ እንዳላቀረቡ ሮይተርስ አመልክቷል፡፡

አሜሪካ ለኔቶ 811 ቢሊየን ዶላር የምታዋጣ ሲሆን ይህም የኔቶ አባል ሀገራት ከሚያወጡት 1 ትሪሊየን 174 ቢሊየን ዶላር 70 በመቶውን ይሸፍናል ተብሏል፡፡

አሜሪካ ይህን አቅም ይዛ እንዴት ለኔቶ ተደምረው እንኳ ከ18 ቢሊየን ዶላር ያልዘለለ የሚያዋጡትን ሦስት ሀገራት ማለትም ፖላንድ፣ ቱርክ እና ግሪክ እንዲተባበሯት ትማጸናለች ሲልም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ደኅንነት ጉዳዮች ተንታኙ ኦመር ኦዝኪዝልኪክ በዚህ ፅሑፍ ይጠይቃል፡፡

ፖላንድ ለዩክሬን መሣሪያ አቅርባለች፤ ቱርክም ድሮኖቿን ሰጥታለች፤ ይህ ከሀገራቱ አቅም እና ስፋት አንጻር ከሚጠበቅባቸው በላይ ተወጥተዋል ለማለት ያስደፍራል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል አሜሪካ የዓለም ኃያል ሀገር እና ሚዛን ጠባቂ እንደመሆኗ የማግባባት ሥራና የላቀ ድጋፍ ለዩክሬን ማቅረብ ሲጠበቅባት እንደ ሌሎቹ ትንንሽ የባልቲክ ሀገራት ሁሉ መሠል አቅርቦቶችን ለመስጠት መሰለፏ ትዝብት ላይ እንደጣላት ቲአርቲ ወርልድ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version