አዲስ አበባ፣ መጋት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በንግድ ሱቆችና በመኖሪያ ቤቶች በተደረገ ብርበራ በሕገ-ወጥ መንገድ ተከማችተው የተገኙ በርካታ ላፕቶፖች፣ ሞባይል ስልኮች እና የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ከ18 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 እና ወረዳ 8 ሶማሌ ተራ እና አሜሪካ ግቢ አካባቢዎች በሚገኙ የንግድ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ላይ ፖሊስ መምሪያው ባደረገው ጥናት እንዲሁም በሕዝብ ጥቆማ እና በተለያየ ጊዜ በሕግ አግባብ በተከናወነ ብርበራ ንብረቶቹ ሊገኙ ችለዋል፡፡
በንግድ ሱቅ እና በመኖሪያ ቤት ሽፋን ከተለያዩ ክፍለ ከተሞችና አካባቢዎች የተሰረቁ ዕቃዎችን ከወንጀለኞች ተቀብለው እንደሚያከማቹ ፖሊስ አስቀድሞ በሰበሰበው መረጃ መሰረት የምርመራ ቡድን በማቋቋም በተደረገ ብርበራ 100 የላፕቶፕ ኮምፒውተሮች እና 13 ሞባይል ስልኮች ተይዘዋል፡፡
በተጨማሪም 1 ሞተር ብስክሌትን ጨምሮ በርካታ የመኪና ስፖኪዮ፣ ፍሬቻ፣ የመኪና ቴፕ እና የተሽከርካሪ መለዋወጫ እቃዎች መያዛቸውን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታነህ በቀለ ገልፀዋል፡፡
18 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከተለያዩ ቦታዎች ተሰርቀው ወደ ክፍለ ከተማው የሚመጡ የግለሰቦችን ንብረት ለማስመለስና ተቀባዮችን በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው ንብረቶች በተለያየ አጋጣሚ የጠፋባቸው እና የተሰረቀባቸው ባለንብረቶች በወቅቱ ንብረታቸው ስለመጥፋቱ ወይም ስለመሰረቁ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ማመልከታቸውን የሚገልፅ ማስረጃ በመያዝ ንብረታቸው መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ እንደሚችሉም ነው የተመላከተው፡፡
በእንዲህ አይነት እኩይ ተግባር ላይ እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኃላፊው ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

