አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ የተዘጋጁትን ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ህጎችን ለመቃወምና እንዳይፀድቁ ለማድረግ እየተደረገ ያለው የትግል እንቅስቃሴ ተጋግሎ ቀጥሏል።
ከሰሞኑ በኒው ጀርሲ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍም በነገው እለት በሳንፍራንሲስኮ፣ በመጪው ሰኞ ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና የበርካታ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች በተገኙበት ይካሄዳል።
የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሽንግተን ዲሲ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መላከህይወት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ሰልፋ ረቂቅ ህጎቹን የሚቃወም ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ምርጫ ድምፅ የሚሰጡ ዜጎች ለተወካዮቻቸው መልእክት የሚያስተላልፋበት ነው ብለዋል።
ግብረሀይሉ ከሰልፋ ባሻገር በሰሜን አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሚያውቁት የምክር ቤት አባል ደብዳቤ በመፃፍ እና ስልክ በመደወል ረቂቁ እንዳይፀድቅ እንዲጠይቁ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ረቂቁ ህግ ሆኖ እንዳይፀድቅ የሚቃወሙ ፊርማ የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት አባል አስኳል ተረፈ በበኩላቸው፥ ረቂቅ ህጎቹ ኢትዮጵያን እስከወዲያኛው የሚጎዱ እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ድጋፍ እንዳይደረግላቸው የሚከለክል ነው ብለዋል።
እንደ ቻይና፣ ቱርክ ሩሲያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ያሉ ወዳጅ ሀገራት ድጋፍ እንዳያደርጉ የሚያስፈራራ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም ምንም አይነት ድጋፍ እንዳያደርጉ የሚያደርግ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጥ የሚያዝ ሲሆን፥ ይህ እርምጃ ደግሞ የእያንዳንዱን ዜጋ ህይወት የሚነካና አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ችግር የሚያባብስ መሆኑን አመላክተዋል።
ምክር ቤቱም ረቂቅ ህጎቹ አንዳይፀድቁ ለማድረግ ከበርካታ ማህበራትና ቡድኖች ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
መንግስትም የዲፕሎማሲ አማራጮችን ተጠቅሞ ረቂቅ ህጎቹ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚጎዱ በመሆኑ እንደማይቀበለው መግለጽ ይገባዋል ባይ ናቸው።
ዜጎችም ይህንን ፀረ ሀገር፣ ፀረ መረጋጋትና የሀገርን ሉዓላዊነትን የሚፃረር ረቂቅ ህግ በአንድ ልብ ሆኖ በሚችለው ሁሉ መታገልና ተቃውሞውን ማሰማት አለበት ብለዋል።
በትእግስት ስለሺ

