አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅና የሀገር ውስጥ ችግሮች ከምንጫቸው እንዲደርቁ ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጥሪ አቀረበ።
ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅና የሀገር ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም አካል የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ጉባዔው አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰሜን አሜሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔውን የጉባዔው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋና የሠባቱ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ አካሂዷል።
በጉባዔው በአሁኑ ወቅት በሚታዩ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶችና መፍትሔውን በተመለከተ ምክክር መካሄዱን የጉባዔው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ለኢዜአ ገልጸዋል።
“በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት በማስተባበር ለጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ በሰላም፣ በፍትሕና በልማት አቅጣጫ በጎ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያመቸን ዘንድ በሂደት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የጉባኤውን ምዕራፍ ለማቋቋም ተስማምተናል” ብለዋል።
“በአሜሪካ ኮንግረስ ሊቀርብ ያለው ኤች አር 6600 እና በሴኔት ሊቀርብ በዝግጅት ላይ ያለው ኤስ 31099 የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚ የሚጎዳና የኩሩውን ሕዝብ ሉዓላዊነት የሚዳፈር ሆኖ ስላገኘነው እንዲቆም ወይም እንዲለወጥ ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ ጥያቄ ለማቅረብ የተስማማን ሲሆን ፥ ምዕመናኑም ይህን ተረድቶ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ለመጠየቅ ተስማምተናል” ሲሉ ገልጸዋል።
በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ በሰሜን፣ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በሌሎችም ተመሳሳይ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈታ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ፣ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ከምንጫቸው እንዲደርቁ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ጥረት እንዲወጡ እንጠይቃለን በማለት አሳስበዋል።
በአገራችን በተለያዩ ሥፍራዎች የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የፍትህ መጓደሎች እንዲቆሙ፣ እንዲወገዙ እና አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ሁሉንም አካል እንጠይቃለንም ነው ያሉት።
በሰሜን አሜሪካ በየቤተእምነቱ የሚገኙ ምዕመናን ባለው ሁኔታ ሳይለያዩ፣ ይልቁንም የገጠመንን አገራዊ ችግር በትብብር መፍታት ይቻል ዘንድ አንድነታቸውን ጠብቀው አምልኳቸውን እንዲፈጽሙ ጠቅላላ ጉባዔው ማመልከቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

