አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ለደቡብ ወሎ ዞን ጤና ተቋማትና ለደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግምታቸው 11 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት “ትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር” በሚለው መርሃ-ግብሩ ነው ድጋፉን ያደረገው፡፡
ሽብርተኛው ህወሓት ባደረገው ወረራ በአማራ ክልል 40 ሆስፒታሎች፣ 450 ጤና ጣቢያዎችና 1 ሺህ 850 ጤና ኬላዎች ዘረፋና ውድመት ደርሶባችዋል፡፡ ከወደሙት ውስጥ 7 ሆስፒታሎች፣ 101 ጤና ጣቢያዎችና 398 ጤና ኬላዎች በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ ናቸው፡፡
በደረሰው ውድመት የጤና ተቋማቱ የአገልግሎት መስተጓጎል ቢገጥማቸውም ወደ ቀድሞ ይዞታቸው ለመመለስና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የ “ፓዝፋይንደር ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ” ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ አስናቀ ÷ ድጋፉ በጦርነቱ የወደሙ ሆስፒታሎች ወደ ተሟላ አገልግሎታቸው እንዲገቡ የሚያስችል እንደሆነና በቀጣይም ድጋፉ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠና የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ ÷ የተደረገው ከፍተኛ ድጋፍ በውድመቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የጤና አገልግሎቶችን የሚያስጀምር በመሆኑ ተናግረው አመስግነዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ ዳኛው በበኩላቸው ፥ ውድመቱን ለመተካትና የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍ በመደረጉ በዞኑ ሕዝብ ስምለአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ምስጋና አቅርበው ፥ ሌሎች የተራድኦ ድርጅቶችም የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

