Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

ካፒቶል ሂል ፊት ለፊት በሚካሄደው ሰልፍ ረቂቅ ሕጎቹ የኢትዮጵያን ሕልውና የሚጎዱ በመሆኑ ውድቅ መሆን አለባቸው የሚሉ መልዕክቶች በሰልፈኞቹ እንደሚተላለፉ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል አስታውቋል።

ረቂቅ ሕጎቹ ለረጅም ጊዜ የቆየውን በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚጎዱ እንዲሁም የሁለቱን አገራት ጥቅም የማያስጠብቁ መሆናቸውን የአሜሪካ መንግስት መገንዘብ እንዳለበት የሚያሳስቡ መፈክሮች እንደሚሰሙም ተገልጿል።

በሰልፉ ላይ በአሜሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በተጨማሪ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል።

በነገው እለት የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ በ”ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021” ወይም ኤስ 3199 ረቂቅ ሕግ ላይ ከሚያደርገው ውይይት እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል።

ኮሚቴው በረቂቅ ሕጉ ላይ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ሊያደርግ የነበረውን ውይይት ማራዘሙ የሚታወስ ነው።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በቅርቡ በኒው ጀርሲ እና በካሊፎርኒያ ግዛት ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በማነጋጋርና ማብራሪያ በመስጠት፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ በማካሄድና ወትዋች (ሎቢስት) በመቅጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

Exit mobile version