Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በህዝብ ህልውና ላይ የሚሰነዘርን ማንኛውንም ጥቃት በጋራ መመከት ይገባል-ብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ህልውና ላይ የሚሰነዘርን ማንኛውንም ጥቃት በጋራ መመከት ይገባል ሲል ብልጽግና ፓርቲ ጥሪ አቀረበ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር የተዘጋጁ ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ህጎችን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በውስጥ ጉዳይዋ ላይ ጣልቃ በሚገቡ የውጭ መንግስታት የተለያየ ጫና እየተደረገባት እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡

የህወሓት ሽብር ቡድን በንጹሃን ላይ ያደረሰውን ጥፋት ከቁብ ያልቆጠሩት አንዳንድ የውጭ አገራት ዛሬም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጸመ ሰበብ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ ሲራወጡ ይስተዋላሉ ብሏል ፓርቲው ፡፡

እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም በአገር ውስጥ፣ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የአገራችንን እውነታ የተገነዘቡ አገራት በጋራ ባደረጉት ሁለንተናዊ ጥረት ብዙዎቹ ሙከራዎች ሊቀለበሱ ችለዋል ነው ያለው፡፡

ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር አዲስ ረቂቅ ወጥቷል ያለው ፓርቲው÷ የኢትዮጵያውያንን መነሳት የማይፈልጉ የተለያዩ ኃይሎችም ረቂቁን ለማፀደቅ ደፋ ቀና እያሉ እንደሚገኙ አመላክቷል፡፡

ይህ ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 በመባል የሚጠራው ረቂቅ በሰሜኑ ጦርነት ትክክለኛ አጥፊው ማን እንደሆነ በሚዛናዊነት ያላየ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል የደረሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እውቅና የማይሰጥ ይልቁንም አንድን ወገን ለመደገፍና እና ለመሸፈን የተረቀቀ ለመሆኑ አመላካች ነው ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ይህ ረቂቅ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረውን ጫና በሚገባ በመገንዘብ ኢትዮጵያውያን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአንድ ላይ በመቆም ረቂቁ እንዳይጸድቅ ጫና ማሳደር እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቧል።

መንግስት የዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመጠቀም የራሱን ኃላፊነት የሚወጣ ሆኖ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ረቂቅ ሰነዱ እንዳይጸድቅ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን መንግስትን ከመደገፍ እና ከመቃወም ጋር ሲያያይዙት እንደሚስተዋሉ የጠቆመው ፓርቲው÷ኤች አር 6600 እና ኤስ  3199 መደገፍ ማለት በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ መፍረድ መሆኑን መዘንጋት አይገባም ብሏል።

ስለረቂቅ ሰነዱ በቂ ግንዛቤ ሳይዙ በግብታዊነት ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን ለመውጋት መጣደፍ ጥፋቱ የጋራ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋልም ነው ያለው፡፡

Exit mobile version