Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት” ጥሪ የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ ምቹ እድል ይፈጥራል -ምሁራን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት” ጥሪ የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ እና ታሪካዊ መስጂዶችና ኢስላማዊ ጥንታዊ ቅርሶችን ለማስጎብኘት ምቹ እድል ይፈጥራል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክና ባህል ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ÷ ይህን መልካም እሴት በማስተዋወቅ የቱሪዝም ገቢን ማሳደግም ሆነ የህዝቦችን ትስስር ማጠናከር ይቻላል ብለዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአንድነት በሚቆምበት የኢድ ወር ኢትዮጵያ ልጆቿን ወደ ሀገር ቤት መጥራቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና አረብ ሀገራት ግንኙነት ተመራማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው÷ በእስልምና ቱሪዝም ውስጥ ሀገሪቱ ያላትን ልዩ ስፍራ እና በእምነቱ ታሪክ ኢትዮጵያ ያላትን ጉልህ ሚና ለተቀረው አለም የምናሳይበት ይሆናል ብለዋል።

በዚህ ጥሪ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ለቱሪዝሙ መነቃቃት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ያነሱት ረዳት ፕሮፌሰር አደም÷ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማሳደግ እና የህዝብ ለህዝብ ትስሰርን ለማጠናከርም መርሃ ግብሩ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ምሁራኑ ይህን አጋጣሚ ወደ በጎ ተጽእኖ ለመቀየር ዳያስፖራ ሙስሊሙ ከአሁኑ ወደ ሀገር ቤት ለመምጣት መወሰን ይገባዋል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ለመርሃ ግብሩ ስኬት ደግሞ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በሀይለየሱስ መኮንን

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version