Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክልሎች ሀብት በማፍራት ለልማት መትጋት ይጠበቅባቸዋል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል መንግስት ፍትሃዊ ልማትን ለማዳረስ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ክልሎች ሀብት በማፍራት ለልማት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር ገለጹ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት የበይነ-መንግስታት ፊሲካል ግንኙነት የሚመራበት አሠራርና ቀጣይ አቅጣጫ በተመለከተ በተካሄዱ ጥናቶች ላይ ውይይት አድርጓል።

በመድረኩ የክልል ርሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር÷ ባለፉት 30 ዓመታት ከመንግስት የሀብት አስተዳደርና ፍትሃዊ የልማት ተደራሽነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ የተጣለበትን ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሪፎርም ጥናቶችን በማካሄድ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

በተለይም የክልሎች በጀት አስተዳደር፣ በክልሎች ውስጥ ያለው የበጀት ድልድል እንዲሁም በክልሎች መካከል ስለሚኖረው የተመጣጠነ እድገት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መድረኩ ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በመጠቆም ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የፌዴራሉ መንግስት ለክልሎች የሚመድበውን ጥቅል በጀት በመቆጣጠር ረገድ የተሻለ ተግባር ማከናወን ቢቻልም÷ ውስን ዓላማ ያላቸውን በጀቶች ለመቆጣጣር የሚያስችል መመሪያ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ይህም ክልሎች የተመጣጣነ እድገትን በሚመለከት ጥያቄ እንዲያነሱ እያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ የወጪያቸውን 40 በመቶ ብቻ በራሳቸው አቅም እንደሚሸፍኑም ነው አፈ ጉባኤው የተናገሩት፡፡

ቀሪው ወጪያቸው በፌዴራል መንግስት እንደሚሸፈን ገልጸው÷ ከዚህ አኳያ ክልሎች ሀብት የመሰብሰብ አቅማቸውን በማሳደግ ለልማት መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ክልሎች ሀብት የመፍጠር አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም ነው የተናገሩት፡፡

ልዩ ዓላማ ያላቸው የፌዴራል ድጎማዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ በፍትሃዊነት ለክልሎች የሚከፋፈልበትን ስርዓት ማበጀት እንዲሁም ሚዛናዊ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

 

በቆንጅት ዘውዴ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version