አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ከ40 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች እስካሁን ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረሳ መሀመድ፥ ከጦርነቱ በፊት ከ90 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደነበሩ ጠቅሰው ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑት እስካሁን እንዳልተመለሱ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱት ትምህርት ቤቶቻቸው በመፍረሳቸው፣ የውሃ፣ የመመገቢያ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶቻቸው በመውደማቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በጦርነቱ በነበረው ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ድምጽና በትምህርት ቤቶቹ ያዩዋቸው ነገሮች የፈጠሩባቸው ስነልቦናዊና ችግሮችም የመማር ፍላጎት እንዲያጡና ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ እንዳደረጓቸው ተነግሯል።
ቢሮው ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችና ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ደገፋ በጦርነት አከባቢ ህጻናት ለከፍተኛ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደሚጋለጡ የተናገሩ ሲሆን÷ ከዚህ ችግር እንዲላቀቁም ስነልቦናዊና ማህበራዊ ምክርና ስልጠና ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

