Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፖለቲካ አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ ሙስና እና ብልሹ አሰራር እንዲንሰራፋ አድርጓል – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ አመራሮች ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ቁርጠኛ ባለመሆናቸው ውጤት ማምጣት እንዳልቻለ የፌደራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የፌደራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን “ሙስናን በመከላከል ረገድ የመገናኛ ብዙኃን ሚና” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ÷ በዓለም ላይ 170 የሚደርሱ አገራት ሙስናን ለመዋጋት የፀረ ሙስና ተቋማት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ተሞክሮዎችም ሙስናን ለመከላከል በመረጃ እና እውቀት ላይ የተመሰረተ ዝርዝር ጥናቶችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተምረናል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሙስናን ለማጥፋት ወንጀሉ ሳይከሰት በፊት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ በመሆኑ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተቀራርበን በመስራት የሞራል ዝቅጠት የገጠማቸውን ሰዎች ማሠልጠን፣ ማስተማር እና ማብቃት አለብን ነው ያሉት፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስን ጨምሮ የፌደራልና የክልል የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች፣ የፌደራል ዕምባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊዎችና የኮሚሽኑ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በሀበኒዮም ሲሳይ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version