አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የአፋር እና የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ለአማራ ክልል የገቢዎች ቢሮ በገንዘብ 10 ሚሊየን ብር እና ግምታዊ ዋጋቸው 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የቢሮ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ ለአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ እና ግምታዊ ዋጋቸው ከ515 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የተለየዩ የቢሮ ቁሳቁሶችን በድምሩ የ15 ሚሊየን ብር እና ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለፁት ÷ ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት ለሁለቱ ክልሎች የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የአሁኑን ድጋፍ ለየት የሚያደርገው በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የገቢ ተቋማትን በማጠናከር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ እንዲያስችላቸው ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ የገቢ ተቋማቱ በሙሉ አቅማቸው ገቢ መሰብሰብ እስኪችሉ ድረስ ቀጣይነት እንደሚኖረው ነው ያረጋገጡት፡፡
የተደረገው ድጋፍ ጉዳት ለደረሰባቸው በየክልሎቹ በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ስር ለሚገኙ የገቢ ተቋማት በፍጥነት እንዲደርስ እና ወደስራ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ጸጋ ጥበቡ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ÷ የገቢ ተቋሙም በሙሉ አቅሙ ገቢ መሰብሰብ እንዲችል ድጋፉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የሚደረገው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሀመድ ሀሰን ÷ ድጋፉ ለቀጣይ ሥራ አጋዥ መሆኑን ገልጸው ድጋፉ ጉዳት ለደረሰባቸው የገቢ ተቋማት በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

