አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቃሊቲ ኢንዱስትሪ መንደር በኤሊያስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 350 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ውድመት መድረሱ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ትናንት ምሽት 3:15 ሰአት ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታዉ ቃሊቲ ኢንዱስትሪ መንደር በኤሊያስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ የእሳት አደጋ ደርሷል። “ከባለንብረቶቹ በደረሰን መረጃ መሰረት 350 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ወድመት ደርሷል” ብለዋል።
በፋብሪካው ያሉት የጨርቅ ማቅለሚያ ኬሚካሎችና በመጋዘን ዉስጥ የሚገኙ ጥሬ እቃዎች እሳቱ ፈጥኖ እንዲስፋፋ ከማድረጋቸዉም በላይ በፋብሪካዉ ቅጥር ግቢ ዉስጥ ለመግባት አመቺ አለመሆኑ እንዲሁም ፋብሪካው ህንጻ ላይ መሆኑ እሳቱን በቀላሉ መቆጣጠር እንዳይቻል አድርጎታል ብለዋል።
በተከናወነው የአደጋ መቆጣጠር ርብርብ ከሌሊቱ 7 ሰዓት እሳቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 15 የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች 6 ውሃ የጫኑ ቦቴዎች እንዲሁም 154 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተዋል፤ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትም 500 ሺህ ሊትር ውሃና 7 ሺህ 800 ሊትር ኬሚካል ፎም ጥቅም ላይ ውሏልም ብለዋል።
የእሳት አደጋዉ በአካባቢዉ ባሉ ሌሎች ፋብሪካዎች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል በዚህ ሂደትም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የተገመተ ንብረት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።
አቶ ንጋቱ እንዳሉት፤ በአደጋ መቆጣጠሩ ሂደት የአየር መንገድና የደብረዘይት እሳት አደጋ ባለሙያዎች እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ የአዲስ አበባ መንገዶችና ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን 6 የውሃ ቦቴ በማቅረብ ተባብረዋል።
በሌላ በኩልም የጸጥታ አካላት አስፈላጊዉን ትብብር ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በስራ ላይ በነበሩ ሦስት የፋብሪካዉ ሰራተኞች ላይ ቀላል ጉዳት የደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ ኢንተርኘራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ ቦታዉ ድረስ በመገኘት በአደጋ ጉዳት የደረሰባቸዉን ባለንብረቶችን ማጽናናታቸውም ተገልጿል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ! ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

