አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተደረገ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የአደሬ ሰፈር የልማትና መረዳጃ ማኅበር የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ 600 ለሚጠጉ የአካባቢው አባወራዎች የማዕድ ማጋራት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የማህበሩ ሰብሳቢ ኑረዲን ረሺድ ÷ ማኅበሩ የማዕድ ማጋራት ድጋፉን ያደረገው በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችና ከአባላቱ ባሰባሰበው 780 ሺህ ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰበት ወቅት አንስቶ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ አቅመ ደካማ ዜጎች ማኅበሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፥ በዛሬው እለት የተደረገው ድጋፍ ለአንድ አባወራ 1 ሺህ 300 መቶ ብር የሚያወጣ ሁለት ኪሎ ቴምር፣ አስር ኪሎ ዱቄት፣ አምስት ኪሎ ገብስ እና አምስት ኪሎ ሩዝ መሆኑንን አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ሼህ ሀሚድ ሙሳ በበኩላቸው ÷ማንኛውም ማኅበረሰብ ከተባበረ፣ ከተቻቻለና ከተረዳዳ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የታላቁን ረመዳን ወር ጾም ምክንያት በማድረግ ለ650 አቅመ ደካማ ወገኖች 1 ነጥብ 62 ሚሊየን ብር በሚገመት ድጋፍ የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባልና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መለስ ዓለም እንደተናገሩት ፥ በተለያየ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ችግሩ ከፍተኛ እንደሆነና ከችግሩ ለመላቀቅ ህዝብና መንግስት በጋራ በመሆን የኑሮ ውድነት በሚያባብሱ ምክንያቶችን መከላከል ይገባል ብለዋል።
ስለተደረገላቸው ድጋፍ ክፍለ ከተማ አስተዳደሩን ያመሰገኑት ተጠቃሚዎቹ ፥ ያለው ለሌለው የማካፈል ባህላችን የበለጠ ሊጎለብት ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

