አዲስ አበባ፣መጋቢት 29፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2013 ሀገር አቀፍ ፈተና እርማት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን በተለመደው ሁኔታ በበይነ መረብ ማስተናገድ መቻሉን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ተናገግረዋል።
ሚኒስትሩ ዛሬ የትምህርት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እና እንባ ጠባቂ ተቋም የይመርመርልኝ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ የባለሙያ ቡድን በመላክ በአገልግሎቱ በአካል በመገኘት ሊኖሩ የሚችሉ ክፍተቶች ዙሪያ የማጣራት ስራ በጋራ መሰራቱን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል።
የፈተና ምዘናና አገልግሎት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎችን ማስተናገድ እንዳለበት እና ተገቢውን ግብረ መልስ እንዲሰጥ አቅጣጫ ተሰጥቶት በመስራት ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሩ ግብረ መልስም እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የፈተናና ምዘና አገልግሎት በበኩሉ 30 ሺህ ተማሪዎች ከፈተና እርማት ጋር በተያያዘ የይመርመርልኝ ጥያቄ ማቅረባቸውን አመላክቷል፡፡
የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በመቅረቱ የዘንድሮው ተፈታኞች ቁጥር ቀድሞ ከነበረው በሁለት እጥፍ አድርጓል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የከፍተኛ ትምህርት የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ ቁጥር በ2013 ዓ.ም 147 ሺህ የነበረውን በ2014 ዓ.ም 5 ሺህ ተማሪዎችን ተጨማሪ እንዲቀበሉ በማድረግ ወደ 152 ሺህ ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በትግራይ ክልል የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪ መቀበል የማይችሉ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ መቆረጡንም ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
በጦርነቱ ሙሉ ሙሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት 50 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ እና እስካሁን ለመልሶ ግንባታ የተሰበሰበው ገንዘብ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብቻ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ከወደሙት ውስጥ የ200 ትምህርት ቤቶች ዲዛይን ተጠናቋል ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣይ ሁለት ወራት ግንባታቸው ይጀመራል ብለዋል።
በዙፋን ካሳሁን

