አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩስያ ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት ራሷን ማግለሏን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነቷን ማቋረጧን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ሩስያ ይህን ውሳኔ ያሳለፈችው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት ፥ የሩስያ ፌደሬሽን ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት እንዲታገድ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው።
ሩስያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተላለፈው የእገዳ ውሳኔ አንድን ሉዓላዊ የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገር ለመቅጣት ታስቦ የተደረገ፥ ህገ-ወጥ እና ፖለቲካዊ ዓላማን ለመጫን የተወሰደ እርምጃ ነው ማለቷን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
“በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በቀጥታ እየተሳተፉ ያሉ አገራት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንደሚከላከል ነፃ ተቋም እራሳቸውን መቁጠራቸው ተቀባይነት የለውም” ያለው የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፥ ሩስያ አሁንም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት የሩስያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ጌናዲ ኩዝሚን በዕገዳ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ በሰጡት አስተያየት፥ የጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ሉዓላዊ አገርን ለማስፈራራት የተወሰደ ህገወጥ ውሳኔ ነው ብለውታል።
ምክር ቤቱም የተወሰኑ አገራትን ፍላጎት ብቻ የሚያራምድ በመሆኑ የዓለምአቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ እያጣ መሆኑን ነው የገለጹት።
በአሜሪካ አነሳሽነት መዘጋጀቱ የተገለጸው ሩስያን ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት የማገድ ውሳኔ በ93 አባላት ድጋፍ፣ በ24 ተቃውሞ እና በ58 ድምፀ ተአቅቦ ነው የጸደቀው፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

