አዲስ አበባ፣ መጋቢት፣ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣይ በምታካሂደዉ አገራዊ ምክክር የትኞቹ ሀገራዊ እሴቶቿን ብትጠቀም የተሻለ ይሆናል በሚለው ጉዳይ ላይ የምሁራን አስተያየት ጠይቀናል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህር ታደሰ መለሰ እና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዋልተንጉስ መኮንን ፥ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ለባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቹ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው በመሆኑ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከውስብስብ ውድቀቶች ያዳኗት እነኝህ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቿ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ ሙሉነሽ ደሴም ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፥ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ መጠሪያዎች የተሰጣቸው ሽምግልና መሰል ዕሴቶች ለአገራዊ ምክክሩና ለብሔራዊ መግባባቱ ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።
ኢትጵያውያን መደበኛ ያልሆኑ የሽምግልና እና የግጭት አፈታት እሴቶች ባለቤት ህዝቦች በመሆናቸው ይህን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን አገራዊ ምክክሩም ይሁን የሚታሰበው ብሄራዊ መግባባት የሰመረ ይሆናል የሚል እምነት እንንዳለቻው ገልጸዋል።
ምክንያቱም እነዚህ እሴቶች በማህበረሰቡ ዘንድ መሰረታቸዉ የፀና፥ ተቀባይነታቸውም የጎላ በመሆኑ መፍትሄያቸውም በሁሉም ወገን ዘንድ ቅቡል በመሆናቸዉ እንደሆነም ነው ምሁራኑ ያብራሩት።
እነዚህ ዕሴቶች የምንፈልገውን ውጤት እንዲያስገኙ ደግሞ በትግበራ ወቅትም ይሁን ከዚያ በፊትና በኋላ ከየትኛውም የፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለባቸው ሲሉም ምክረ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
በሙሀመድ አሊ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

