Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሐረሪ ክልል ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ 60 አመራሮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 60 የወረዳ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ እንደገለፁት ፥ በተለይም ፓርቲው ባካሄደው 1ኛ ጉባኤ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች እና ከህዝቡ ጋር ባደረገው ውይይት የተነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ እርምጃ ተወስዷል፡፡

በነባሮቹ ቦታ ላይ የተተኩት አዳዲስ አመራሮችም ህዝቡን በማወያየትና ለጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ተጨባጭ የለውጥ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ ዘርፎች ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ የተለያዩ ግብረ ሃይሎች ተቋቁመው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አመራሩ ህዝቡን በእኩል በማየት የአመራር ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ያሳሰቡ ሲሆን ፥ ፓርቲው የጀመረውን የማጥራት ስራም በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለፀው፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከልም 22 አመራሮች ከኃላፊነት ሲነሱ፣ አስሩ ከደረጃ ዝቅ የተደረጉ ሲሆኑ ፥ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ ከከፍተኛ እስከ ቀላል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን የገለፁት ደግሞ በክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጃፋር አሊዪ ናቸው፡፡

አዳዲስ የተመደቡ አመራሮች ምደባ የተካሄደው የትምህርትና ስራ ብቃትን ያማከለ እና ከጎሰኝነትና ከሙስና አመለካከትና ተግባር በፀዳ መልኩ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

አዳዲስ የተመደቡ አመራሮች የትምህርትና የስራ ብቃትን ያማከለ እና ከጎሰኝነትና ከሙስና አመለካከትና ተግባር የሚፀየፉ መሆናቸው ታይቶ ምደባው መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

ለአዳዲስ አመራሮችም በዛሬው እለት ወደ ሰራ እንዲሰማሩ የስራ መመሪያ መሰጠቱም ነው ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version