አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ”ስፖርት ለሰላም ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የ2014 ዓ.ም የክልሎች እና የክለቦች የውሃ ዋና ሻምፒዮና መካሄድ ተጀመረ።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሠረት ደምሱ የስፖርት ልዩ ባህሪያት ሰላምን ለማስፈን ፣ መቻቻልን ለማምጣት፣ የሃገር ፍቅርን፣ ማህበራዊ እና የልማት ትስስር ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
ይህ ሻምፒዮና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት እና ለ2022 አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
በሻምፒዮናው የአማራ ፣ የሲዳማ ፣ የጋምቤላ ክልሎች እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የኦሮሚያ ፖሊስ ውሃ ዋና ስፖርት ክለብ፣ የቢሾፍቱ ከተማ መስተዳድር ውሃ ዋና ስፖርት ክለብ፣ ዳዊት እምሩ ህንፃ ተቋራጭ የውሃ ዋና ስፖርት ክለብ እና ሳምሶን ኃ.የተ. የግ. ማህበር ውሃ ዋና ስፖርት ክለብ ተሳታፊዎች ናቸው ።
በሁለቱም ፆታ በነፃ ቀዘፋ፣ በጀርባ ቀዘፋ፣ በደረት ቀዘፋ ፣በቢራቢሮ ቀዘፋ፣ በድብልቅ ቅብብል ፣ በነፃ ቅብብል፣ በቅልቅል- ድብልቅ ቅብብል፣ በቅልቅል- ነፃ ቅብብል እና በግል ድብልቅ የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩ በተለያዩ የስፖርት ካታጎሪዎች የሚደረግ ነው።
በመክፈቻው ቀን በተደረገው 4 በ200 ሜትር ነፃ ቀዘፋ የሴቶች የፍፃሜ ውድድር አማራ ክልል 1ኛ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ 2ኛ እና ቢሾፍቱ ከተማ 3ኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል።
ሻምፒዮናው ዛሬን ጨምሮ እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2014 ዓ.ም የሚደረግ ይሆናል።

