Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአማራ እና ቅማንት ብሔረሰብ የጋራ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አብሮነታችንን በማጠናከር ወደ ቀደመ ሰላማችን እንመለሳለን” በሚል መሪ ቃል የአማራ እና ቅማንት ብሔረሰብ የጋራ ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ፥ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጋሻው አለማየሁ እንደተናገሩት÷ በእርስ በርስ ግጭቶች ንፁሀን ዜጎች ህይወታቸው አልፏል፣ ሰላማቸውን አጥተዋል፣ ከቀያቸውም ተፈናቅለዋል።
ይህ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት የሆነውን የቅማንት ፅንፈኛ ቡድን በጋራ በመታገልና ያለፈው ይብቃ በማለት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሩን መፍታት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ቢክስ ወርቄ÷ አንዱን ህዝብ ለሁለት በመክፈል የግል ጥቅማቸውን ለማጋበስ የሚጥሩ ቡድኖችን ማህበረሰቡ ሊታገላቸው ይገባል ብለዋል።
የሰው ልጅ ከመረዳዳት አልፎ በጠራራ ፀሀይ ሲገዳደል ለምን ብሎ መታገልና ለመፍትሄ ተዋናይ መሆን ከሁሉም አካል የሚጠበቅ እንደሆነም ተናግረዋል።
“መገዳደሉን፣ ጭካኔውን፣ መፈናቀሉን፣ መሰደዱንና መጎዳቱን አይተነዋል፤ ያተረፍነው ነገር የለም” ያሉት አቶ ቢክስ ወርቁ፥ የቀረን ቢኖር ዳግም መተባበርና አብሮነት ነውና ወደ ሰላም በር ገብቶ ለሁለንተናዊ ለውጥ መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጠገዴ አርማጭሆ በጎ አድራጎት ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አሰማራው መኮነን በበኩላቸው÷ ከዚህ ቀደም ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችን በማካሄድ አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው፥ የዛሬው ምክክርም በሁለቱ ወገኖች ያሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
በሙሉጌታ ደሴ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version